
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ እዝ እና የሰሜን ምዕራብ እዝ አባላት ሰላምን ከማስከበር ሀገራዊ ግዳጃቸው ባለፈ በልማት ሥራዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በማጠናከር “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል።
የምሥራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽን ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ ሠራዊቱ የተሰጠውን ሀገር የመጠበቅ አደራ በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ በብቃት እየተወጣ ነው ብለዋል። የሠራዊቱ ዋነኛ ግዳጅ የሀገርን ሉዓላዊነት፣ ዳር ድንበር፣ የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት መጠበቅ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ሠራዊቱ ችግኝ ሲተክል ሰላምን እያወጀ መኾኑንም አብራርተዋል። “ሰላም መኾኑ የሚገለጸው ጦርነት ባለመኖሩ ወይም ጥይት ባለመተኮሱ ብቻ አይደለም” ያሉት ሜጄር ጄኔራሉ ሀገርን በማልማት እና የነገ ተስፋን በመሰነቅ ሠራዊቱ የበኩሉን ብሔራዊ ግዴታ እየተወጣ ነው ብለዋል።
ወጣቱ ለማይጠቅም ዓላማ ከመሰለፍ ይልቅ ለቀጣዩ ትውልድ ሀገራዊ ክብር እና ዝናን በሚያስቀጥሉ የልማት ተግባራት ላይ እንዲሳተፍም ጠይቀዋል። በተለይም የጦርነትን አስከፊነት ሳይናገሩ ወጣቱን ወደ ጥፋት የሚገፉ እና ሁከት የሚሰብኩ አካላት መኖራቸውን ጠቁመዋል። ንቁ የኾነው የዘመኑ ወጣት በዚህ ማታለያ ውስጥ እንዳይወድቅ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ ሰላም እና ዕድገት አቅጣጫ እያመራች መኾኗን የገለጹት ሜጄር ጄኔራሉ እዚህም እዚያም የሚታዩ ሁከት የመፍጠር ሙከራዎችን ሠራዊቱ ከሕዝብ እና ከመንግሥት ጋር በመኾን በጽናት እንደሚሻገራቸው አረጋግጠዋል። “ማንም ኢትዮጵያን ሊያንበረክክ አይችልም” በማለት ሠራዊቱ ሀገርን የማስቀጠል የጸና አቋሙን በተግባር እንደሚያረጋግጥ
ተናግረዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ እዝ የደረጃ ሦሥት ሆስፒታል አዛዥ ኮሎኔል ዶክተር ታደግ አበራ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊደርስባት የሚችለውን ተጽዕኖ እና ተጋላጭነት ለመከላከል፣ የደን ሽፋንን ለመጠበቅ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።
መከላከያ ሠራዊቱ አካባቢን ከተለያየ ጉዳት በመጠበቅ እና በመንከባከብ ሀገርን የማልማት እና የመለወጥ ጽኑ ፍላጎት እንዳለውም ገልጸዋል።
ሠራዊቱ የሕዝብን ደኅንነት ከመጠበቅ ባሻገር በበጎ አድራጎት እና በልማት ሥራዎች ላይ በስፋት መሳተፉ ከሕዝባዊ ባሕሪው የሚመነጭ ነው ብለዋል። ለሕዝብ እና ለሀገር ካላቸው ጥልቅ ፍቅር እና ክብር በመነሳት በማንኛውም ጊዜ ማኅበረሰቡን እና ሀገርን በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ ሠራዊቱ ወደኋላ እንደማይል ተናግረዋል።
ሠራዊቱ በተፈጥሮም ኾነ በሰው ሠራሽ አደጋዎች ጊዜ ከሕዝቡ ጎን በመቆም ሕዝቡ ሲያለማም አብሮ በማልማት ሕዝባዊነቱን በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ እና ይህ አኩሪ ተግባሩም ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
የሠራዊቱ አባላትም የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክበው ለጥቅም እንደሚያበቁ አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
