የሀረሪ ክልል በ2019 በጀት ዓመት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየሠራ ነው።

5
በሀረሪ ክልል ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ውድነቱን በዘላቂነት ለማረጋጋት ታቅዶ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የክልሉ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር እና የግብርና ልማት ቢሮ ኀላፊ ሮዛ ኡመር ገልጸዋል።
ምክትል ርእሰ መሥተዳድር እና የግብርና ልማት ቢሮ ኀላፊዋ በ2019 በጀት ዓመት በክልሉ ሊከናወኑ የታቀዱ ዋና ዋና የልማት ሥራዎችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም አርሶ አደሮች የክረምት ወቅትን ብቻ ጠብቀው ከሚሠሩት የግብርና ልማት ተላቅቀው ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞችን እንደ አማራጭ እንዲጠቀሙ ለማስቻል የግብዓት አቅርቦት፣ የመሬት ዝግጅት እና የሙያተኛ አቅም ማጎልበት ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የግብርና ልማትን በማሳደግ ረገድ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የገለጹት ወይዘሮ ሮዛ በተለይም ዓመቱን ሙሉ መልማት የሚችለውን በቆሎ በበጋ እና በበልግ ወቅቶች የማልማት ሥራ ሲከናወን መቆየቱን ጠቅሰዋል።
ለምሳሌም ባለፈው 2018 የበጀት ዓመት 2ሺህ 160 ሄክታር መሬት በበቆሎ ተሸፍኖ እንደነበር አስታውሰዋል።
በተያዘው አዲስ በጀት ዓመትም የሰብል ምርትን ለማሳደግ የያዟቸውን ዕቅዶች ሲያብራሩ እንዳሉት፦
✍በመኸር እርሻ 11 ሺህ 956 ሄክታር መሬት በዘር የሚሸፈን ሲኾን ከዚህ ውስጥ 2ሺህ 378 ሄክታር መሬት በበቆሎ ምርት ብቻ እንደሚሸፈን ነው ያስረዱት።
✍ የስንዴ ልማትም በሄክታር ከነበረበት 32 ኩንታል በያዝነው በጀት ዓመት ወደ 33 ኩንታል በማሳደግ 14 ሺህ 850 ኩንታል ምርት ይሠበሠባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
✍ በበልግ እና መኸር እርሻ የዝናብ እጥረትን ተቋቁመው በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ የማሽላ እርሻ ሥራዎች በእጥፍ እንዲያድጉ ይደረጋልም ብለዋል።
✍ 4 ሺህ 700 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ልማት የተለያዩ የአትክልት እና ሥራሥር ተክሎች እንደሚሸፈን እና በከተማ ግብርና ደግሞ 537 ሄክታር መሬት እንደሚሸፈን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የእንስሳት እና ዓሳ ምርት እና ምርታማነትን በልዩ ትኩረት ለማሳደግ ሥራዎች እንደሚሠሩ ተመላክቷል።
አርሶ አደሮችን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እና በገጠሩ አካባቢ የሌማት ትሩፋት መርሐግብር ውጤታማነትን ለማሳደግ 18 የዶሮ መንደሮች እንደሚመሠረቱም አስገንዝበዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ 600 ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች የሚከናወኑ ሲኾን፣ በክልሉ ተረጂነትን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር እና የግብርና ልማት ቢሮ ኀላፊ ሮዛ ኡመር በመግለጫቸው አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሀገራዊ ምክክር እና ሀገር በቀል ዕውቀት
Next article“ወጣቶች አሻራቸውን በትውልድ ተሻጋሪ ልማት ላይ ማሳረፍ ይኖርባቸዋል” ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ ረጋሳ