
ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ፣ ቱባ ባሕል እና ኅብረ ብሔራዊነት የገነባች ውብ ሀገር ናት። ነገር ግን የዘመናት ባለጸጋ ኾና ሳለ ሀገሪቱ በተለያዩ ታሪካዊ ወቅቶች ከግጭት እና ከአለመግባባት አዙሪት ሙሉ በሙሉ መላቀቅ አልቻለችም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ችግሮቿን በራሷ ጥበብ የማጥራት እና የማስተካከል ጽኑ አቅም ያላት ሀገር ናት።
በባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ላይ የተመሰረተው የሀገር ሽማግሌዎች ሚና እና አሁን እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሰላም ግንባታ ምሰሶዎች ኾነው ጎልተው ይታያሉ።
“ሰማይ ቢቀደድ ሽማግሌ ይሰፋዋል” የሚለው የአበው ብሂል በባሕላዊ ሥርአታችን ውስጥ የሽምግልናን ሚና ከፍ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
በአማራ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ ሠብሣቢ መርጌታ ብሩህ ዘላለም እና ምክትል ሠብሣቢ አቶ ይመር ሰይድ እንደሚገልጹት ሽማግሌዎች በአካባቢያቸው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ያለ ወጭ እና ጉልበት በሰላማዊ መንገድ ሲፈቱ ኑረዋል፤ ዛሬም እንዲሁ ይሠራሉ።
የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ግጭቶችን አስቀድሞ በመከላከል፣ የተጣሉትን በማስታረቅ እና የተኳረፉትን በማቀራረብ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት የመፍታት ባሕልን በማስረጽ ረገድ ትልቅ ኀላፊነት እየተወጡ ይገኛሉ።
ይህ የሀገር በቀል ዕውቀት ማኅበረሰቡ የሰላሙ ባለቤት እንዲኾን እና የሰላም ችቦው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የሚያደርግ የቁርጠኝነት ማሳያ ነው።
ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች በየአካባቢያቸው ስኬታማ ቢኾኑም የኢትዮጵያን ዘመን ተሻጋሪ እና አጠቃላይ ሀገራዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ ግን የላቀ እና ሁሉን አቀፍ ምክክር ይጠይቃል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ እንዳሉት የኮሚሽኑ መዋቅርና ዝግጅት ሲሠራም ኾነ ሲቀረጽ አሁንም ወደ መጨረሻው የሀገራዊ ምክክር ሲገባ መሠረት ያደረገው ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከምሁራን በተቀዱ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ላይ ነው።
ይህም ማለት ዘመናዊው ሀገራዊ ምክክር ከባሕላዊው የእርቅ ተሞክሮ ተነጥሎ የሚታይ ሳይኾን የአባቶች የውይይት እና የመደማመጥ እሴት በሰፊው እና በብሔራዊ ደረጃ የሚደገምበት ትልቅ ምዕራፍ ነው። አጀንዳዎችን በግልጽነት በመወያየት፣ ያለፈውን ቁስል አክሞ አዲስ ማኅበራዊ ውል መፍጠር ለሀገሪቱ መጻኢ ዕድል ወሳኝ ነው።
የአካባቢ ሽምግልናዎች ለብሔራዊ ምክክር ሂደቱ ትልቅ የግብዓት ምንጭ ናቸው። ከቤተክርስቲያናት፣ ከመስጊዶች፣ ከዕድሮች እና ከማኅበረሰቡ መዋቅሮች የሚነሳው የሰላም ጥሪ ደግሞ መላው ሕዝብ በሂደቱ ውስጥ እኩል ተሳታፊ እንዲኾን ያደርጋል።
የኢትዮጵያ ችግሮች በውይይት፣ በሠለጠነ ሃሳብ እና በጋራ መግባባት እንደሚፈቱ በማመን፣ መጻኢ ዕድሏን ብሩህ ለማድረግ ትልቅ ታሪካዊ ዕድል ተከፍቷል።
ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ፈተናዎች በራሷ ልጆች ጥበብ፣ በባሕላዊ እሴቶቿ እና በዘመናዊው የምክክር ማዕቀፍ አሸንፋ ሰላሟን ታረጋግጣለች፤ ለቀጣዩ ትውልድም አስተማማኝ ሀገር ታሻግራለች።
#አሚኮ #NationalDialogue #Ethiopia #ሀገራዊምክክር #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_20_2018_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
