ለጋራ ሰላም በጋራ መቆም በመቻሉ ውጤት ተገኝቷል።

3

 

በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰንበቴ ከተማ የአፋር ክልል ዞን አምስት እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አጎራባች ወረዳዎች የመሪዎች ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አሊ ሰይድ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ሰላሙን ለማጠናከር በየጊዜው በሰላም ካውንስሎች በኩል ሕዝባዊ ውይይቶችን በማድረግ ችግሮች እንዳይከሰቱ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል። በዚህም ውጤት መምጣቱን አስታውቀዋል።

በአፋር ክልል የሰሙሮቢ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሀሰን መሐመድ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በትብብር እየተሠራ ነው ብለዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ጀማል አሊ ሁለቱ ሕዝቦች የተዋለዱ እና ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። በቀጣናው ያለው ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

በቀጣይ የቀጣናውን ሰላም በማረጋገጥ አጎራባች ሕዝቦችን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር በትኩረት እንደሚሠራም አሥረድተዋል።

በአፋር ክልል የዞን አምስት ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሀሰን ሙሳ በቀጣናው ሰላምን ለማደፍረስ የሚሠሩ ኀይሎች ላይ የሕግ ማስከበር ሥራ በጋራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የሁለቱ ሕዝቦች አብሮነት በማይናወጥ መሠረት ላይ የተገነባ በመኾኑ ይህን የሚያጠናክሩ ተግባራት በትብብር ለመሥራት መግባባት ላይ መደረሱም ተመላክቷል።

#አሚኮ #ስላም #ኢትዮጵያ 🇪🇹

#ከሚሴ #ነሐሴ_20_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ:-ይማም ኢብራሒም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article” አለማለፍ” የማይታወቅበት የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት