የዓባይ ባንክ እጆች – 5ሺህ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ

7
ዓባይ ባንክ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን ለመወጣት እና የትምህርት ዘርፉን ለማገዝ በኢኮኖሚ ጫና ምክንያት የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ለተቸገሩ ተማሪዎች የሚኾን 50 ሺህ ባለ 50 ገጽ ደብተሮችን ለአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስረክቧል።
በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባንኩ የስትራቴጂ ዋና መኮንን ወንዲፍራው ታደሰ ባንኩ ከተቋቋመበት 15 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተወዳዳሪ ባንክ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ይህን ዕድገት የሚመጥን ሰፊ የማኅበራዊ ኀላፊነት የመወጣት ሥራዎችን ሲያከናውን እንደቆየም ገልጸዋል።
እንደ መጀመሪያ ምዕራፍ ፕሮጀክት የተዘጋጁት እነዚህ 50 ሺህ ደብተሮች 5ሺህ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ይኾናልም ብለዋል።
በቀጣይም ድጋፉ በስፋት እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ባንኩ ከዚህ ቀደም ጣና ሐይቅን ከእምቦጭ አረም የመታደግ፣ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን የመደገፍ እና ከፍተኛ ውጤት ላመጡ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ዕውቅና እና ማበረታቻዎችን መስጠትን ጨምሮ በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ ቢሮው “አንድ ደብተር ለአንድ ተማሪ” በሚል የተማሪዎች ደብተር ለማሠባሠብ አስተላልፎት የነበረውን ጥሪ አክብሮ ዓባይ ባንክ ላደረገው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።
በክልሉ በነበረው ሁኔታ ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን እና በሺህዎች የሚቆጠሩ የትምህርት ተቋማት አለመከፈታቸውን ጠቅሰዋል።
ይህን ችግር በመንግሥት ብቻ መፍታት ስለማይቻል ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት እና ባለሃብቶችም የባንኩን አርዓያነት ተከትለው ከመማሪያ ደብተር ባሻገር ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
✍️ ዘጋቢ:- ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“በባዕዳን ተልዕኮ ያልተሰናከለው የኢትዮጵያ ስኬት”