
ኢትዮጵያ የተረጋጋ ሰላም አግኝታ ብሔራዊ ጥቅሟን እንዳታስከብር እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷን እንዳታፋጥን የባዕዳን ተልዕኮ ተሸካሚዎች ጫና ለማድረግ እየሠሩ ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ጂኦ-ፖለቲካዊ መጠናከር፣ የቀይ ባሕር ተፅዕኖዋ ማደግ እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብን የመሰሉ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ማሳካቷ ይከነክናቸዋል።
የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ የውጭ ጥቅመኛ ኀይሎች እና ታሪካዊ ጠላቶች ትክክለኛነቱ ባልተረጋገጠ የሚዲያ ፕሮፓጋንዳ ተጠምደዋል።
የባዕዳን ሴራ በኢትዮጵያ ላይ የተጀመረው ደግሞ ዛሬ አይደለም። ከዓድዋ ድል በፊት እና በኋላ የነበሩ የቅኝ ግዛት ሙከራዎች፣ በ1920ዎቹ የፋሺስት ጣሊያን ወረራ እና በየዘመናቱ የነበሩ የድንበር እና የዓባይ ውኃ ውዝግቦች ዋነኛ ማረጋገጫዎች ናቸው።
በአሁኑ ወቅት የቴክኖሎጂውን ዕድገት ተንተርሰው የሕዝብን ስሜት የሚቀሰቅሱ እና ጥላቻን የሚያስፋፉ ሀሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጩ ይገኛሉ።
በራሳቸው ሕዝብ ላይ የውስጥ ግጭቶችን በመቀስቀስ የግል ጥቅማቸውን እያሯሯጡም ነው። ለታጠቁ ቡድኖች የገንዘብ፣ የሚዲያ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ በማቅረብ በሀገሪቱ ግጭቶች እና አለመግባባቶች እንዲባባሱ መሥራታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መናገራቸው ይታወሳል።
የእነዚህ የባዕዳን ተልዕኮ ተሸካሚዎች የመጨረሻ ዓላማ ኢትዮጵያ ጠንካራ እና ማዕከላዊ መንግሥት እንዳይኖራት ማድረግ፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ማዳከም እና በመጨረሻም ሀገሪቱን በማፍረስ በቀጣናው የራሳቸውን ጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት ማስከበር እንደኾነም በንግግራቸው አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟ እንዳይከበር እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ እንዳይፋጠን የሚፈልጉ የውስጥም ኾነ የውጭ ጠላት ኀይሎች እንዳሉም ገልጸዋል።
ሻቢያ እና ሕገወጡ ሕወሃት ባረጀ እና ባፈጀ ስልት ኢትዮጵያን ለማዳከም ዛሬም እንደ ትላንቱ በቅዠት ምኞት ላይ ይገኛሉ ብለዋል። ይሁን እንጅ እንኳን “ሕወሃት፣ ሻቢያ እና ሱዳን ቀርተው ሌላ አካል ቢጨመር በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ቅንጣት ታክል ስጋት የለንም” ሲሉ ነው ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ጥቅማቸው ላይ ጠንካራ መኾናቸውን የጠቆሙት።
የትኛውንም የሀሳብ ልዩነት በኀይል ለመፍታት የሚደረግ ልምምድ እና የባንዳነት አመል ትላንትም ነበር ዛሬም አለ ነው የሚሉት። እነዚህ ኀይሎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የፋይናንስ እና የሎጅስቲክ ድጋፍ ያደርጋሉ፤ ነገር ግን መቸውንም ቢኾን በየትኛውም መንገድ ኢትዮጵያን አይደፍሯትም ብለዋል።
በተለይ በግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ እየታየ ያለው ውጤት ለባንዳ እና ለባዳዎች የእራስ ምታት ቢኾንም ተጠናክሮ የሚቀጥል እንጂ የሚቆም አለመኾኑን ገልጸዋል።
ማንኛውንም ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል ጠንካራ የሀገር መከላከያ ኀይል መገንባቱንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የባዕዳን እና የባንዳ ሴራ ሳይበግራት ሕዳሴ ግድብን ማስመረቅ ችላለች። አሁንም ሀገሪቱ 30 ቢሊዮን ዶላር ወጭ በማድረግ ትውልድ ተሻጋሪ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ትገኛለች።
ለአብነትም ሀገሪቱ የጋዝ ፋብራካን ከማስመረቅ ባሻገር የነዳጅ ማጣሪያ፣ የቢሾፍቱ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ እና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ትገኛለች።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
