
የዓለማችንን የአየር ንብረት መዛባት ለመቀልበስ በሚደረገው ታላቅ ሩጫ ውስጥ የቻይናው “ታላቁ አረንጓዴ ግንብ” እና የኢትዮጵያው “አረንጓዴ ዐሻራ” የተፈጥሮን ውበት እና የሰው ልጅን ቁርጠኝነት ያሳዩ ህልውናን የማስቀጠል ግብግቦች ናቸው።
በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1970ዎቹ መገባደጃ ላይ የተጀመረው እና “ታላቁ የአረንጓዴ ግንብ” በመባል የሚታወቀው የቻይናው የሰሜናዊ አካባቢዎች የደን ጥበቃ ፕሮግራም በዓለማችን ላይ ከተካሄዱት ትላልቅ የተፈጥሮ መልሶ ማቋቋም ሥራዎች መካከል አንዱ እንደኾነ ይነገራል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በዋናነት በሰሜናዊ ቻይና የሚገኘውን የጎቢ በረሃ መስፋፋትን ለመግታት፤ የአሸዋ ማዕበልን ለመቀነስ እና የእርሻ መሬቶችን ከአፈር መሸርሸር ለመጠበቅ ያለመ ነበር።
ፕሮጀክቱ በተተገበረባቸው በርካታ ቀጣናዎች ውስጥ የአረንጓዴ ሽፋን መጠንን በከፍተኛ ሁኔታ ለመጨመር ያስቻለ ሲኾን በተለይም ቤጂንግን ጨምሮ በዋና ዋና የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ይከሰቱ የነበሩትን አደገኛ የአሸዋ እና የአቧራ ማዕበሎች ድግግሞሽ እና አስከፊነት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉ በስኬታማነቱ ተጠቃሽ እንደኾነም ይነሳል።
ቻይና የጎቢ በረሃን መስፋፋት ለመግታት ያስጀመረችው ግዙፍ ፕሮጀክት የአንድ ወቅት ዘመቻ ሳይኾን ከ10 ዓመት በላይ የዘለቀ የትውልድ ቅብብሎሽ እንደተከናወነበትም ይገለጻል።
የቻይና ሳይንቲስቶች ለአካባቢው አስቸጋሪ የአየር ንብረት ተስማሚ የኾኑ ሀገር በቀል ዛፎችን በመምረጥ እና የተተከሉትን ችግኞች ዕድገት በጥብቅ በመከታተል የበረሃውን ጉዞ መግታት ችለዋል።
ተሞክሮው ግዙፍ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ያሉባቸውን እምቅ አቅም እና ውስብስብ ፈተናዎች ለዓለም የሚያሳይ ሲኾን በረሃማነትን ለመዋጋት ለሚፈልጉ ሌሎች ሀገራትም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ኾኖ ተተግብሯል።
ከሁሉም በላይ ግን የደን ልማቱን ከሕዝቡ የኑሮ መሻሻል፤ ከኢኮ-ቱሪዝም እና ከፍራፍሬ ልማት ጋር በማያያዝ ማኅበረሰቡን የአረንጓዴ ልማቱ ዋነኛ ባለቤት ማድረግ ችለዋል።
ኢትዮጵያም በተመሳሳይ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሯ በሰፊ ሕዝባዊ ንቅናቄ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ለትውልድ የሚሻገር የአረንጓዴ ልማት ባሕልን ማስረጽ ከጀመረች ውላ አድራለች።
በዚህ ሀገራዊ የልማት አቅጣጫ ላይ ስንት ችግኝ ተተከለ? ከሚለው የቁጥር ሽፋን ባሻገር ስንት ችግኞች ጸደቁ? በሚለው ላይ ትኩረት በማድረግ በየደረጃው የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ እና የመጠበቅ ልምድን ማሳደግ ላይ መሠረታዊ ተግባርን ይጠይቃል።
በመኾኑም ማኅበረሰቡ ከተተከለው ዛፍ ላይ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያገኝ እና ዛፎችን በሚገባ መጠበቅ ይችል ዘንድ አሁንም ከዚህ በላይ ሥራ ይጠይቃል።
ቻይና ከ10 ዓመታት በላይ ለፍታ ባካበተችው የአረንጓዴ ልማት ተሞክሮ ያስመዘገበችውን ውጤት ኢትዮጵያም በታላቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ እና በሀገር በቀል ዕውቀት በመታገዝ እውን ማድረግ ችላለች።
አረንጓዴ ልማት ሀገርን የማልበስ ብቻ ሳይኾን የዜጎችን ሕይወት የመቀየር ታላቅ አቅም እንዳለውም የሁለቱ ሀገራት ውጤታማ ተሞክሮ ሕያው ማረጋገጫ የሚኾን ነው። በመረጃ ምንጭነት ነጋሪት ጋዜጣን እና ሌሎች ድረገጾችን ተጠቅመናል።
#Ameco #አረንጓዴ_ዐሻራ #GreenLegacy
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_19_2018_ዓ_ም
✍️ በሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
