ከመጽሐፍ ሽያጭ ለትምህርት ቁሳቁስ ማሟያ፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አርዓያነት።

6

 

​📖​ የትምህርት ተዳራሽነትን እና ጥራትን ለማረጋገጥ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይሰናከሉ ማድረግ የመጀመሪያው ወሳኝ ጉዳይ ነው።

በተለይም በኢኮኖሚ ምክንያት ደብተር፣ እስክርቢቶ፣ እርሳስ፣ቦርሳ፣ ዩኒፎርም እና የመሳሰሉትን ቁሳቁሶች ማሟላት ለማይችሉ ተማሪዎች የሚደረግ ድጋፍ የወደፊት እጣ ፈንታቸውን በመቀየር በኩል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች የመደገፍ ሥራ ተራ የበጎ አድራጎት ተግባር ሳይኾን የነገዋን ኢትዮጵያ በዕውቀት የተገነባች ለማድረግ የሚጣል መሠረታዊ ኢንቨስትመንት ነው። 📚

ይህ ተግባር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል ደረጃ በክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራዎች በዕቅድ ውስጥ በማካተት በንቅናቄ እየተሠራበት ይገኛል። ንቅናቄው ሁሉንም ዜጋ የሚጠይቅ ተግባር ነው።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ.ር) “ጽናት” የተሰኘ መጽሐፍ ጽፈው ከሰሞኑ ለንባብ አብቅተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በመጽሐፉ ምረቃ ወቅት እንደተናገሩት የመጽሐፉ የመጀመሪያ እትም ሽያጭ 50 በመቶ ለተቸገሩ ሕጻናት ተማሪዎች ለ2019 የትምህርት ዘመን የትምህርት ቁሳቁስ ማሟያ የሚውል እንዲኾን ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን “አንድ ደብተር ለአንድ ተማሪ” በሚል እየተተገበረ በሚገኘው ክልላዊ ንቅናቄ የፕሬዝዳንቱ ተግባር ለሌሎችም ምሁራን፣ መሪዎች እና ደራሲዎች አርዓያ የሚኾን ነው ብለዋል።

ዶክተር አስራት አፀደወይን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በኩል የትምህርት ዘርፉን በተለያየ መንገድ ሲደግፉ እንደቆዩ ጠቁመዋል። አሁንም በግላቸው የመጽሐፉን ሽያጭ 50 በመቶ ለተማሪዎች የቁሳቁስ ማሟያ ድጋፍ በማድረጋቸው ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።

የፕሬዝዳንቱ ተግባር ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው፣ ለትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ለሚደረገው ርብርብ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

🎓 የዛሬ ምሁራን የትናንት ተማሪዎች ነበሩ ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ለነገ የተማረ ትውልድ ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ የመሪዎች፣ የምሁራን፣ የባለሃብቶች እና የአጋር ድርጅቶች ተሳትፎን ይፈልጋል ነው ያሉት።

ለዚህም የተማሪዎችን ቁሳቁስ ለማሟላት በሚደረገው ጥረት ሊሳተፉ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

​#Ameco #Education
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_19_2018 ዓ_ም

✍️ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየመደጋገፍ እና የወንድማማችነት እሴት፤ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሀረሪ ክልል።
Next articleየበረሃውን ጉዞ ያስቆመው አረንጓዴ ግንብ፤ የቻይና ተሞክሮ እና የኢትዮጵያ “አረንጓዴ ዐሻራ”