
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደጋገፍ እና የወንድማማችነት እሴትን በሚያጠናክር መልኩ ተጠናክሮ መቀጠሉን በብልጽግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
በክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌቱ ወዬሳ በሰጡት መግለጫ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የኅብረተሰቡን ገንዘብ፣ ጉልበት እና ዕውቀት በማስተባበር በራስ አቅም የመልማት ዕድልን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ትኩረት የተሰጠው ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም የኅብረተሰቡ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በማቃለል ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት።
በክልሉ በተጀመረው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎትም የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፤ በችግኝ ተከላ፤ በነጻ ሕክምና አገልግሎት፤ ደም በመለገስ፣ የትምህርት ቤት ቁሳቁስ ድጋፍ በማሰባሰብ፤ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመገንባት እና በማደስ እንዲሁም ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ማዕድ ማጋራት፤ አዲስ እና ነባር የመማሪያ ክፍል ግንባታ እና እድሳት፤ የትምህርት ቤቶች የተማሪ ወንበሮች ጥገና፤ ጽዳት እና ውበት ሥራዎችን ጨምሮ የማጣቃሻ መጻሕፍት የማሰባሰብ ሥራ በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ ከ344 ሺህ በላይ ማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
በጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በእርስ መተሳሰብን እንዲሁም ሁለንተናዊ ትብብር እና መተጋገዝን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የዜጎችን አብሮነት እና ወንድማማችነት የበለጠ እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የገለጹት ኀላፊው በዘንድሮው መርሐ ግብርም ይህንን እሴት በተግባር በሚያሳይ መልኩ እየተተገበረ ስለመኾኑ ገልጸዋል።
የተጀመረው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ የተለዩ የትኩረት መስኮችን መነሻ ያደረገ እና ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ በሚችል አግባብ እንዲፈጸም የክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
#Ameco #በጎ_ፈቃድ #VolunteeringEthiopia🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_19_2018 ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
