🌱 አረንጓዴ አሻራ፤ ከችግኝ ተከላ ዘመቻነት ወደ ዘላቂ የኢኮኖሚ እና የሥነ-ምሕዳር ግንባታ!

5

 

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተራ የችግኝ ተከላ ዘመቻነት አልፎ ወደ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ እና የሥነ-ምሕዳር ግንባታ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል። ባለፉት ሰባት ዓመታት የተተኩሉ ችግኞች የሀገሪቱን የደን ሽፋን ከ23 በመቶ በላይ አሳድገውታል፤ ይህ ሀገራዊ ንቅናቄ በቁጥር ብቻ ሳይኾን በጥራትም እያደገ መጥቷል።

የኅብረተሰቡን ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማዕከል በማድረግ እየተሠራ በመኾኑ ውጤቱ በተግባር እየተገለጠ ነው።

በአማራ ክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደን ምርምር ዳይሬክተር እና ከፍተኛ ተመራማሪ ምናለ ወንዴ (ዶ.ር) አሁን ላይ ያለው የችግኝ ተከላ ከሁለንተናዊ የተፋሰስ ልማት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው ብለዋል። በላይኛው ተፋሰስ የሚሠሩ ሥራዎች ታችኛውን የሚታደጉ መኾን አለባቸው፤ ይህም አፈርን ከጥፋት ከመታደግ እና እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ ሀብቶች በደለል እንዳይሞሉ ከመከላከል፤ የአየር ንብረት መዛባትን በመቋቋም የማይበገር አረንጓዴ ልማት ጋር በቀጥታ ይተሳሰራል ነው ያሉት። ለዚህም ነው ዛፍ መትከል አሁን ላይ የህልውና ጉዳይ ኾኖ እየተሠራበት ያለው ብለዋል።

የጽድቀት ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉም የመርሐ ግብሩ ሌላው ትልቁ የስኬት ማሳያ አድርገው አንስተዋል። ከሕዝብ ንቅናቄው ባሻገር ለችግኞች ጥራት እና እንክብካቤ እየተሰጠ ባለው ከፍተኛ ትኩረት በአማራ ክልል የጽድቀት መጠኑ እስከ 82 በመቶ መድረሱን ተመራማሪው የክልሉን ግብርና ቢሮ መረጃ ዋቢ በማድረግ አንስተዋል።

በሂደቱ የባለቤትነት ጉዳይ ትልቅ ትኩረት መሰጠት እንደሚኖርበት ግን ይጠቁማሉ። በግለሰብ ደረጃ የሚተከሉ ችግኞች ጽድቀታቸው እጅግ ከፍተኛ እንደኾነ አስታውቀዋል። በአንጻሩ በማኅበረሰብ ወይም በመንግሥት ቦታዎች የሚተከሉት ግን አሁንም የተሻለ ክትትል እና የከሰሙትን የመተካት ሥራ ይፈልጋሉ ነው ያሉት።

ግለሰቦች ከምርቱ የሚያገኙትን ጥቅም አስልተው መንከባከባቸው የተሻለ ጽድቀት እንዲኖራቸው ማስቻሉን የገለጹት ተመራማሪው የጋራ ቦታዎችንም የዚሁ ዓይነት የባለቤትነት ስሜት በሚፈጥር መንገድ ማሥተዳደር ለውጤት እንደሚያበቃ ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራው የምግብ ዋስትናን እና ግብርናን የማዘመን ሚናው የጎላ እንደኾነም ተመራማሪው ያስረዳሉ። እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝና ፓፓያ ያሉ የፍራፍሬ ችግኞች ሲተከሉ በቀጥታ የማኅበረሰቡን የአመጋገብ ሥርዓት እና የምግብ ዋስትና የሚያሻሽሉ ናቸው ብለዋል።

የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ከማልማት ባለፈ ናይትሮጅን አማቂ ዛፎችን በመትከል አፈርን በማዳበር ለሰብል ልማት ምቹ ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል። በተለይም በቤት ዙሪያ ዛፍን ከሰብል እና ከእንስሳት ጋር በማቀናጀት የሚተገበረው የጥምር ደን ግብርና የኅብረተሰቡን ገቢ ለማሳደግ፤ የማገዶ ችግርን ለመፍታት እና በደጋማው አካባቢ በስፋት የሚታየውን የእንስሳት መኖ እጥረት ለመቅረፍ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ለሀገር በቀል ችግኞች ትኩረት መስጠት ይገባል ያሉት ተመራማሪው በተለይም ችግኞችን በዕውቀት እና በሙያ ላይ ተመስርቶ መትከል እንደሚገባ አስታውቀዋል። ለአብነት ወይራ በተፈጥሮው የሌሎች ዛፎችን እንክብካቤ ስለሚፈልግ ይህንን ተረድቶ ትክክለኛውን ሥነ-ምሕዳር መርጦ መትከል እንደሚገባም አንስተዋል። እንደ ኦስትሪያ ያሉ ሀገራት ለጣውላ የሚጠቀሙበት ዛፍ ለመድረስ 80 ዓመታት እና ከዚያም በላይ የሚፈጅ ሲኾን የኛዎቹ ሀገር በቀል ዛፎች ግን በተገቢው እንክብካቤ አንጻራዊ በኾነ መልኩ ፈጣን ዕድገት የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አካባቢን በአረንጓዴ ከማልበስ አልፎ ለምግብ ዋስትና፣ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ለንጹሕ አየር እና ለዘላቂ ሥነ-ምሕዳር መሠረት የሚጥል ሳይንስን የተመረኮዘ የትውልድ ፕሮጀክት ኾኖ መቀጠል ይኖርበታል ነው ያሉት።

#አሚኮ #GreenLegacy #Ethiopia🇪🇹
#ባሕር_ዳር ሐምሌ_19_2018 ዓ_ም

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየምክክሩ ስኬታማነት፤ ከሀገራዊ መግባባት እስከ ቀጣናዊ መረጋጋት 🌍🕊️
Next articleየሀገር መከላከያ ሠራዊት ጽንፈኞች የዘረፏቸውን የሕጻናት አልሚ ምግቦች እና ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር አዋለ።