
🇪🇹 ኢትዮጵያ በስፋቷ፣ በሕዝብ ቁጥሯ እና በጂኦፖለቲካዊ መገኛዋ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የጀርባ አጥንት እንደመኾኗ በኢትዮጵያ የሚፈጠረው ዘላቂ ሰላም ለጎረቤት ሀገራትም ዋስትና የሚሰጥ ነው።
በአንጻሩ በሀገሪቱ የሚፈጠር ማንኛውም የውስጥ አለመረጋጋት ለጎረቤት ሀገራት የሚተርፍ የዜጎች ስደት፣ የድንበር ተሻጋሪ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ እና የንግድ መስመሮች መስተጓጎልን ያስከትላል።⚠️
ሰሞኑን እየተካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ስኬት ከኢትዮጵያ አልፎ ለምሥራቅ አፍሪካ እና ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም፣ መረጋጋት እና ጠንካራ ትስስር ወሳኝ ጠቀሜታ አለው።
ሀገራዊ ምክክሩ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ውጥረት መፍቻ ብቻ ሳይኾን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን የፖለቲካ ስነ-ምህዳር ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር ስትራቴጂካዊ እርምጃ እንደኾነም ታምኖበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በምክክር ጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በውስጧ ሰላም ስታረጋግጥ፣ ለቀጣናው እና ለመላው አፍሪካ የምታበረክተው ሰላም ማስከበር እና ልማት አበርክቶው በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሙሐመድ ድሪር የሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ለሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ የሚኾን ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን የምታስተሳስር ማዕከል በመኾኗ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ስኬት በቀጣናው ላሉ ሀገራት ጭምር ስኬት እንደኾነ ገልጸዋል።
በቀጣናው የሰላም እና መረጋጋት መስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስረድተዋል። ለመላው አፍሪካ ሀገራት ትልቅ ተሞክሮ የሚኾን የታሪክ አካል መኾኑንም አንስተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ፣ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ “ሀገራዊ ምክክሩ እጅግ በጣም ስልታዊ ነው፤ ምክንያቱም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳንኾን ለቀጣናው እና ለአሕጉራችን ጠቀሜታ አለው” ብለዋል።
“ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካ መፍትሔ” የሚለውን መርሕ በተግባር የሚፈጽም እንደኾነም አመላክተዋል።
#አሚኮ #ሀገራዊ_ምክክር #Nationaldialogue
✍️ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
