
1 ሺህ 501ኛው የመውሊድ በዓል በደሴ ከተማ ሸዋ በር ሕዝባዊ ኢስላማዊ ትምህርት ቤት በድምቀት ተከብሯል።
የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ ሼህ አሊ ሰይድ በሰደቃ ፕሮግራሙ ላይ አብሮነትን እና አንድነትን እንዲያንጸባርቅ እና የሃይማኖት መከባበርን ለማጎልበት የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮችም የሰደቃው ተካፋይ ኾነዋል ነው ያሉት።
ኡስታዝ አሕመድ አሊ በዓሉ የዕዝነት ነብይ የኾኑት ነብዩ መሐመድ ( ሰ.ዐ.ወ) ሰላም እና ዕዝነት በእርሳቸው ላይ ይዘው በመወለዳቸው እና አላህ ነብይ አድርጎ ስለላካቸው የምናመሰግንበት በዓል ብለዋል።
ነብዩ የተላኩት ለዓለማት ዕዝነት ነው፤ ወሎም የአብሮነት እና የመከባበር ተምሳሌት በመኾኗ በደሴ ከተማ በዓሉ ሲከበር የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ወገኖችን ታሳቢ በማድረግ እንደኾነ ገልጸዋል።
ለአሚኮ አስተያየታቸውን የሰጡት የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ የኾኑት ፈለቁ ዓለማየሁ ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ መውሊድ ሲከበር የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እርድ ሲፈፅሙ እኛንም አስበው ያደርጋሉ ብለዋል። ይህ አብሮነት ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አንስተዋል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ የበዓሉ ታዳሚዎች የመውሊድ በዓል ለነብዩ ያለንን ውዴታ የምናሳይበት፤ አክብሮት እና ፍቅራችንን የምንገልጽበት ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ከድር አሊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
