እውነተኛው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ፍቅር የሚገለጸው የእርሳቸውን ርህራሄ በተግባር በመኖር ነው።

4
1 ሺህ 501ኛው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ በዓል በባሕር ዳር ከተማ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሠብሣቢ ሼህ መሐመድ ሰይድ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወደዚህ ምድር ከመምጣታቸው አስቀድሞ ለዓለማት ሁሉ ዕዝነት ኾነው እንደሚላኩ የተበሰረላቸው እንደኾነ ተናግረዋል።
የመውሊድ በዓል ይህንን ታላቅ ጸጋ በማሰብ በየዓመቱ በድምቀት እና በልዩ ደስታ የሚከበር የላቀ የምስጋና በዓል መኾኑን አስገንዝበዋል።
በዓሉን ስናከብር እያንዳንዱ አማኝ አቅሙ በፈቀደ መጠን ያዘጋጀውን ማዕድ ለምስኪኖች፣ ለወዳጅ ዘመድ እና ለጎረቤት በማካፈል አብሮነቱን እና ደስታውን በተግባር ሊገልጽ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከማኅበራዊው በጎ አድራጎት ባሻገር በነሺዳ፣ በመንዙማ፣ በሐድራ፣ በግጥም እና በተለያዩ ማሞገሻዎች የነብዩን ታላቅነት ማውሳት የበዓሉ ልዩ መንፈሳዊ ድምቀት መኾኑን ጠቁመዋል።
በተለይም በእነዚህ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶች ላይ የሚደረጉ ዱዓዎች፣ የሚለገሱ የሕይወት ምክሮች እና ስለ መልካም ሥነ-ምግባር የሚሰጡ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ለሃይማኖቱ ተከታዮች በመንፈሳዊነት በማነጽ ረገድ የጎላ ፋይዳ እንዳላቸው አብራርተዋል።
የሰላም በር መስጊድ ኢማም ሼህ ሙሐመድ አብራር እውነተኛው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ፍቅር የሚገለጸው መውሊድን በመሳሰሉ በዓላት ብቻ ሳይኾን በዕለት ከዕለት ሕይወታችን የተቸገሩትን በማገዝ እና የነብዩን ርህራሄ በተግባር በመኖር ነው ብለዋል።
የሃይማኖቱ ተከታዮች ለአንድነት እና ለሀገር ሰላም ዘወትር ዱዓ ማድረግ እና መተጋገዝ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በተለይም የሃይማኖት አባቶች (ዑለሞች) የነብዩን ዕዝነት፣ ፍትሐዊነት እና የሰላም እሴቶች በቃል ብቻ ከማስተማር ይልቅ በተግባር በመኖር ለሕዝቡ እውነተኛ አርዓያ ሊኾኑ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየመውሊድ በዓል በታላቁ አንዋር መስጊድ
Next article“የአብሮነት መውሊድ በደሴ”