
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በምክክር ጉባኤው ሂደት ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የምክክር ጉባኤው መክፈቻ ከተደረገ በኋላ ከሐምሌ 9/2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም ድረስ የምክክር ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
መጀመሪያዎቹ ላይ ተሳታፊዎች በእያንዳንዱ ቡድን ኾነው ስለምክክሩ ሂደት፣ ስለሥነ ዘዴዎቹ፣ ስለ ሥብሠባ ሥነ ሥርዓት እና የመሳሰሉትን ካብላሉ በኋላ በቀጣዮቹ ቀናት ተከፋፍለው በሚገባ በመተዋወቅ በየተሰጧቸው አጀንዳዎች ላይ የመተዋወቅ እና የመግባባት ሂደት አድርገዋል ብለዋል።
በሂደቱ ክርክር አሳልፈዋል ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ በምክክር ሂደት ክርክር እና ጭቅጭቅ አስፈላጊ እና የሚጠበቅ ነውም ብለዋል።
እስካሁን ሂደቱ በጣም ጥሩ መኾኑንም ገልጸዋል። የሚያጋጥሙ የልዩነት ሀሳቦች እና ስሜቶች በሂደት እየተቀራረቡ ሲሄዱ ወደ ሁለተኛው የምክክር ሂደት ይገባሉ ነው ያሉት። በዚህ ሂደት ከተለያዬው የምክክር ሂደት ወደተቀራረበው ሂደት የሚገቡት እና በመጨረሻም ወደ ሦሥተኛው እና የመግባባት ሂደት የሚገቡትም በዚህ መልኩ መኾኑን ተናግረዋል።
ተሳታፊዎች የምክክር ተሳትፏቸው በመከባበር እና በመደማመጥ ላይ የተመሠረተ መኾኑን አንስተዋል። በዚህ ሂደት አስተባባሪዎች፣ ምሁራን እና ባለሙያዎች የዕውቀት ግብዓት በመስጠት ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸውም ብለዋል። አመካካሪዎች ከራሳቸው ስሜት ነጻ ኾነው ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም እየተደረገ መኾኑን አስረድተዋል።
የምክክሩ ሂደት ከዚህ መድረሱ በራሱ የምክክር ጉባኤውን አዋጭነት ያመላክታል ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን አራት ሺህ ሰዎች ያለልዩነት በአንድ አዳራሽ ተከባብረው እየተመካከሩ ነው ብለዋል። በሂደቱ ውስን ልዩነቶች ቢፈጠሩ እንኳን የምክክር ሂደትን ገና እየተለማመድን መኾናችንን ከግምት ማስገባት ይገባል ነው ያሉት።
ስምንት አጀንዳዎች የተመረጡት ከ200 ሺህ በላይ ከኾኑ አጀንዳዎች መኾኑን አስታውሰዋል።
ኹሉም ቡድኖች በኀላፊነት በተሰጣቸው አጀንዳዎች ላይ እየተመካከሩ ነውም ብለዋል። ይህ ሥነ ዘዴም በተለያዩ ሀገራት ታይቶ ውጤት የተገኘበት መኾኑንም አንስተዋል። አካሄዱም ትክክለኛ እንደኾነ እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
#Ethiopian #NationalDialogue #የኢትዮጵያሀገራዊምክክር
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ:- አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
