🚨 ሰላምን በማደናቀፍ እና በተከበብኩኝ ትርክት ሕልውናን በሕዝብ ደም የማቆየት የሕገ ወጡ ሕወሃት አባዜ 🩸🛑

13

 

ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ከማዕከላዊ ሥልጣን ከተወገደ በኋላ ወደ መጣበት የትጥቅ ትግል ሥነ-ልቦና በመመለስ፣ የትግራይን ሕዝብ እንደ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መከታ እየተጠቀመበት ይገኛል። ይህ አካሄድ የአማፂያን የቅስቀሳ እና የሽፋን ስትራቴጂ ተብሎ ከሚጠራው ጽንሰ-ሀሳብ ጋር የሚያያዝ እንደኾነ ዓለም አቀፋዊ ትንታኔዎች ያሳያሉ።

የተቀናሽ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ማኅበር ፕሬዝዳንት ፲ አለቃ ደጀኔ ሸዋረጋ ያረጋገጡትም ቡድኑ እንደ 1982 እና 1983 ዓ.ም በአማራ ሕዝብ እና ወጣት ትከሻ ላይ ተራምዶ ሥልጣን መያዝን ቀዳሚ ዓላማው እንዳደረገ ነው።

ቡድኑ በ1960ዎቹ መጨረሻ ሲመሠረት ጀምሮ የተከተለው የጠባብ ብሔርተኝነት ትርክት ሁልጊዜም ውጫዊ ጠላት እንዲፈልግ የሚያስገድደው ነው።

የራሱን የፖለቲካ ኪሳራ ለመሸፈንም ሕልውናውን ከትግራይ ሕዝብ የሕልውና አደጋ ጋር በማስተሳሰር ሕዝቡን የከበባ ሥነ-ልቦና ውስጥ ከቶታል። በዚህም ወጣቱን በማስገደድ ወደ ጦርነት እንዲገባ በማድረግ ሕገወጥ ቡድኑ የመኖር ሕልውናውን እያራዘመ ነው።

የቡድኑ የሕልውና ማስጠበቂያ ስትራቴጂ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተፈጻሚነትም ፈተና ውስጥ ጥሎታል። ስምምነቱ ደም አፋሳሹን ጦርነት በማስቆም ለኢትዮጵያም ኾነ ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ ታሪካዊ ዕድል የፈጠረ ነበር።

፲ አለቃ ደጀኔ ሸዋረጋ እንደሚሉት ግን ሕገ ወጡ ሕወሃት ተፈናቃዮችን እንደ መጫወቻ ካርድ እየተጠቀመ የሕዝቡን ሰላም እያደፈረሰ ነው።

የቡድኑን ድርጊት በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ስቴፈን ስቴድማን (ዶ.ር) በዳበረው የሰላም አደናቃፊዎች ዕይታ መሠረት የሰላም ስምምነት የፖለቲካ ሥልጣናቸውን፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን ወይም ፍጹም የበላይነታቸውን የሚቀንስባቸው መሪዎች ስምምነቱን ለማፍረስ ሰበብ ይፈልጋሉ። ሕወሃትም ሰላም ከሰፈነ ሕዝቡ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን ማንሳቱ ስለማይቀር ተፈናቃይ አልተመለሰም በሚል የውሸት ትርክት ቀውሱን ማራዘም ለህልውናው ወሳኝ አድርጎ እየተጠቀመበት ነው።

ቡድኑ አሁን ላይ ከፖለቲካ ፓርቲነት ይልቅ በጥቂት ልሂቃን እና ቤተሰቦች ወደተጠለፈ “የግል ማኅበር” መቀየሩን ፲ አለቃ ደጀኔ ሸዋረጋ ጠቁመዋል። በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነቱን ያጣው እና ከትግራይ ሕዝብ ሰፊ ፍላጎት የተነጠለው ይህ ሕገ ወጥ ቡድን መደበኛ የመንግሥት በጀትን በማጣቱ ራሱን በገንዘብ የሚደግፈው በሕገ-ወጥ ንግድ ነው።

፲ አለቃ ደጀኔ ሸዋረጋ እንዳነሱት የትግራይን ወርቅ በሕገ-ወጥ መንገድ መሸጥ፣ ወጣቶችን ለሱዳን ጦርነት አሳልፎ መስጠት እና ከስደተኛ ካምፖች ወታደሮችን መመልመል ቡድኑ የተዘፈቀበት አሳሳቢ የጦርነት ኢኮኖሚ መገለጫዎች ናቸው።

በፕሮፌሰር ፖል ኮሊየር የስግብግብነት እና ቅሬታ ንድፈ-ሀሳብ መሠረት ይህ የተፈጥሮ ሀብት ብዝበዛ እና የሰው ልጅን እንደ ሸቀጥ የመገበያየት ተግባር ቡድኑ ለሰብዓዊ መብትም ኾነ በጄኔቫ ስምምነት ለተደነገጉ ዓለም አቀፍ ሕጎች ደንታ እንደሌለው ያሳየ ነው፤ ለሞራላዊ እና ፖለቲካዊ ውድቀቱም መረጋገጫ ኾኖ ይነሳል።

ሕገ ወጡ ሕወሃት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ ወደ ሰላማዊ ፖለቲካ ከመቀየር ይልቅ ሕዝብን እንደ መከታ፣ ጦርነትን እንደ ዕድሜ ማራዘሚያ፣ የውሸት ትርክትን ደግሞ እንደ ፖለቲካ መሳሪያ መጠቀሙን ቀጥሏል። በመኾኑም ቡድኑ ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ፣ ፕሪቶሪያ የመለሰለትን የትግራይን ሕዝብ የሰላም ተስፋም እያጨለመ በመኾኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ኾነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊታገሉት ይገባል።

#አሚኮ #Peace #Ethiopia #PretoriaAgreement

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየተዋበው ጀጎል የሀረርን ቀደምት ሥልጣኔ እየመሰከረ የሀገርንም ገጽታ እየገነባ ይገኛል።
Next article“ቆሻሻን ተጠይፎ የሚያስወግድ ትውልድ ተፈጥሯል” ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ