
መንግሥት ካስቀመጣቸው አምስት ቁልፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምሰሶዎች መካከል አንዱ የኾነውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ በታሪካዊቷ የሀረር ከተማ ሰፊ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑ ተገልጿል።
ጥንታዊ ውበቷን ከዘመናዊ ገጽታ ጋር በማሰናሰል አዲስ ገጽታን የተላበሰችው ሀረር አሁን ላይ እየተተገበረ ባለው የኮሪደር ልማት እና የቅርሶች እድሳት ሥራ የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ማነቃቃት ችላለች።
የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሀብት የኾኑት የሀረር ጀጎል ጥንታዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲለሙ እና ለትውልድ እንዲተላለፉ መደረጉ የ”መደመር” እሳቤ ያመጣው ህያው ትሩፋት መኾኑ ተመላክቷል።
ይህ በዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት ለአደጋ ተጋልጠው የነበሩ ቅርሶችን ከማዳኑም ባሻገር የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋት እና የጎብኝዎችን ቆይታ በማራዘም ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ አቅም በእጅጉ አሳድጎታል።
በክልሉ የተከናወኑት ስኬታማ የቱሪዝም ማጎልበት ተግባራት፣ ከውጭ ሀገር ቱሪስቶች በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች እና የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ሐረርን በስፋት እንዲጎበኙ እና አስደናቂ ውበቷን ለዓለም እንዲያስተዋውቁ ሰፊ ዕድል ፈጥሯል።
የመደመር ትውልድ የትናንትን ታሪክ ከዛሬ ጋር በማስተሳሰር፣ ከትናንት ወረቶቻችን መልካሙን ወስዶ በማላቅ፣ የዛሬውን ጥረት አክሎበት ለነገው ትውልድ የሚያኮራ ቅርስ እያስተላለፈ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ትናንት የነበሩንን ጠንካራ ነገሮች ሳናፈርስ፣ ያለፈውን ስብራት ጠግነን በማብቃት የተሠራው ታሪክ ትውልድ የማይዘነጋው አኩሪ ገድል መኾኑ ተጠቁሟል። በአዲስ መልክና ቀለም የተዋበው ጀጎል የሀረርን ቀደምት ሥልጣኔ እየመሰከረ የሀገርንም ገጽታ እየገነባ ይገኛል።
#አሚኮ #HararJugol #EthiopiaTourism #CorridorDevelopmentHistoricalHeritage
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
