
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ታሪካዊ የለውጥ ጉዞ ላይ ትኩረቱን ያደረገ “ጽናት” የተሰኘ የመጽሐፍ ምረቃ መርሐ ግብር በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።
መጽሐፉ የጎንደር ዩንቨርሲቲን ከ1947 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም ያለውን ተካሪካዊ የለውጥ ጉዞ የሚያትት ነው።
“ጽናት” መጽሐፍ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ.ር) የተጻፈ ሲኾን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ነው በጎንደር ከተማ እየተመረቀ የሚገኘው።
ለጸሐፊው የበኩር ልጅ መኾኑ የተነገረለት መጽሐፉ በ386 ገጾች ተቀንብቦ ነው ለአንባብያን የቀረበው።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። ጥሪ የተደረገላቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች እና የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞችም ታድመዋል።
በመጽሐፉ ምረቃ ላይ ተገኝተው ስለ መጽሐፉ ዳሰሳ ያቀረቡት የቀድሞው የጎንደር ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ “ጽናት” የተሰኘው መጽሐፉ ታሪካዊ ብቻም ሳይኾን ውርስ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በ70 ዓመታት ሂደቱ ውስጥ ያሳለፈው ውጣ ውረድ የተገለጸበት መንገድ በታሪክ የሚቀመጥ ኾኖ ስለማግኘታቸው ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ ተናግረዋል።
በመጽሐፉ የመጀመሪያ ምዕራፎች ላይ ዘመናዊ ትምህርትን ከሀገር በቀል ጋር ማዋሀድ እንደሚገባ መጽሐፉ መግለጹ በሀገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ የትምህርት ተቋማት ሀገር በቀል ዕውቀት ላይ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ዘመናዊ ትምህርትን ከሀገር በቀል ዕውቀት ጋር አዋህደው የተጓዙ ሀገራት የተሻለ ዕድገት መፍጠር ስለመቻላቸውም አንስተዋል።
ሌላኛው በመጽሐፉ ላይ አስተያየት ያቀረቡት የቀድሞው የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር በላይ ካሣ መጽሐፉ በመግቢያው ላይ ዩኒቨርሲቲው እንደተቋም የተቋቋመበትን ዓላማ እና የቆመበትን ጽናት መግለጹን ጠቁመዋል።
የመጽሐፉ አዘጋጅ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ.ር) በዩንቨርሲቲው አመራርነት ላይ ግልጽ የኾነ እና በመተማመን ላይ የተመሠረተ አመራር እንደነበራቸው በመጽሐፉ ላይ ገልጸዋል። ይህ የአመራርነት ብቃት ተቋምን ወደፊት ማሻገር እንደሚችል ማሳያ ነውም ብለዋል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች ተቋማት ጋር ያለው ጠንካራ ግንኙነት ለዩኒቨርሲቲው ስኬት ቁልፍ አስተዋጽኦ እንደነበረው መገለጹ ተቋሙ አሁን ለደረሰበት ስኬት እንዲደርስ አድርጓል ነው ያሉት።
ዶክተር አስራት የጻፉት ጽናት የተሰኘው መጽሐፍ የዩኒቨርሲቲውን ታሪክ እና የለውጥ ጉዞ ከመከተብ ባሻገር ቀጣይ መሪዎች በሁሉም ዘርፍ የተሳሉ መኾን እንደሚገባቸው በመድረኩ ተገልጿል።
#AMECO #GondarUniversity #Ethiopia
#ጎንደር፡ ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ:- ደስታ ካሣ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
