የታየው እና የተሰማው ሁሉ አይታመንም!

7

 

ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአኹኑ ወቅት በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ኾነ በሀገራችን በስፋት እየተስተዋለ የመጣው የሳይበር ስጋት “ዲጂታል ምስል እና ድምፅ ማጭበርበር” (Deepfake Technology) ነው::

ዲጂታል ምስል እና ድምፅ ማጭበርበር ማለት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የአንድን ሰው ትክክለኛ ገፅታ፣ ድምፅ ወይም የእንቅስቃሴ ቪዲዮ በከፍተኛ ጥራት አስመስሎ በመሥራት፣ ያላላቸውን ንግግሮች እንዳሉ አስመስሎ ማቅረብ ወይም ያልተገበሩትን ድርጊት እንደፈፀሙ አድርጎ ማሳየት ነው።

ቀደም ሲል እንደነዚህ አይነት ሃሰተኛ ምስሎችን ወይም ቪዲዮዎችን በቀላሉ መለየት ይቻል ነበር፤ በአኹኑ ወቅት ግን ቴክኖሎጂው እጅግ በመራቀቁ ምክንያት የተሰራጨው ምስል ወይም ድምፅ እውነተኛ ይኹን ሀሰተኛ ለመለየት አዳጋች ኾኗል።

በሀገራችን የዲጂታል ፋይናንስ እና የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ከመጣበት ኹኔታ ጋር ተያይዞ፣ ይህ አሠራር በሦስት ዋና ዋና ዘርፎች ትልቅ ስጋት መደቀኑን የኢንሳ መረጃ እማኝ ነው።

#የፋይናንስ ማጭበርበር፦የቅርብ ዘመድ ወይም ወዳጅን ድምፅ በ AI አስመስሎ በመሥራት (Voice Cloning) “አስቸኳይ ችግር ገጥሞኝ ነው” በሚል በቴሌብር ወይም በሞባይል ባንኪንግ ገንዘብ ማታለል፤

#ማኅበራዊ ውጥረት መፍጠር፦ የታዋቂ ሰዎችን ወይም የመንግሥት ኅላፊዎችን ገፅታ እና ድምፅ በመጠቀም ሕዝብን የሚያጋጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨት፤

#የግለሰቦች ስም ማጥፋት፦የሰዎችን ፎቶ አግባብ ከሌላቸው ምስሎች ጋር በማቀናጀት ስም የማጥፋት እና የማስፈራራት ድርጊቶችን መፈፀም።

ማጭበርበርን እንዴት እንለይ እና እንከላከል?

✍️በስልክ ደውሎ ማረጋገጥ፦ በድምፅ መልዕክት ወይም በቪዲዮ ገንዘብ እንዲላክ ከተጠየቁ፣ ወዲያውኑ መደበኛ የስልክ ጥሪ በማድረግ ትክክለኛነቱን ያረጋግጡ፤

✍️ምንጭን ማረጋገጥ፦መረጃዎችን ከይፋዊ የመንግሥት እና ከታመኑ የመገናኛ ብዙሃን ገፆች ያረጋግጡ፤

✍️ጥንቃቄ ያድርጉ በቪዲዮዎች ላይ ከተፈጥሮ ውጭ የኾኑ የአይን፣ የከንፈር ወይም የድምፅ መዛነፎችን በጥንቃቄ ያስተውሉ፤

✍️ከማጋራት መቆጠብ፦ ያልተረጋገጡ እና አጠራጣሪ ቪዲዮዎችን ወይም የድምፅ ፋይሎችን ለሌሎች ከመላክ መቆጠብ፤

በመጨረሻም፦የታየውን እና የተሰማውን ሁሉ ወዲያው አለማመን እና ከማጋራት በፊትም ማረጋገጥ ተገቢ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከጠመንጃ ፖለቲካ ወደ ምክክር ባሕል የሚደረግ የፖለቲካ ሽግግር 🤝
Next articleጤናማ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።