
ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁ መሠረታዊ የሚባሉ የፖለቲካ፣ የታሪክ እና የዕይታ ልዩነቶች የሚንጸባረቁባት ሀገር ናት። እነዚህን ልዩነቶች በንግግር እና በምክክር ከመፍታት ይልቅ ኀይል እና ጠመንጃ ምርጫ ኾነው ሀገሪቱን ለከፋ ችግር ሲዳርጓት ቆይተዋል። ከዚህ ችግር ለመውጣት ደግሞ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ምክክሩም ታሪካዊ ስብራቱን በመጠገን የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከጦርነት አዙሪት ወደ ምክክር ባሕል ለማሸጋገር ትልቅ ተስፋ ጥሎበታል። የጋራ መግባባት በመፍጠር እና ሰላማዊ ፖለቲካን በማንበር በኩል የሚኖረው አስተዋጽኦም ቀላል አይደለም። መሠረታዊ በኾኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር አንደኛው አስተዋጽኦ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መረጃ ሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዓላማው በዜጎች እና በፖለቲካ ኀይሎች መካከል የታጡ የጋራ እሴቶች፣ የታሪክ ትረካዎች እና የሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ዕይታዎች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር ነው። ግጭቶች የሚጀምሩት በሀሳብ ልዩነት ብቻ ሳይኾን ሀሳብን በነፃነት የሚያስተናግድ እና የሚያስማማ መድረክ በማጣትም ነው።
ኮሚሽኑም እነዚህን መሠረታዊ ችግሮች በመለየት እና ታሳቢ በማድረግ ሁሉንም ወገን ያሳተፈ የጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ እየሠራ ይገኛል።
ከጦርነት ወደ ንግግር የተቀየረ የፖለቲካ ባሕል ሽግግር ማድረግም ሌላኛው አስተዋጽኦው ነው። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ በኀይል ሥልጣን የመያዝ ወይም የመቀማት ባሕል የተጫነው ነው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ደግሞ ይህንን አጥፊ አዙሪት ሰብሮ አሸናፊ እና ተሸናፊ የሚለውን አደገኛ የፖለቲካ አካሄድ በማስቀረት የጋራ የአሸናፊነት አስተሳሰብን የሚያጎለብት የፖለቲካ ባሕል ይገነባል። በጠመንጃ አፈሙዝ ሥልጣን ወይም መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ በሀሳብ የበላይነት የማመን ባሕል እንዲጎለብት መንገድ ይጠርጋልም።
ምክክሩ ዘላቂ ሰላም እና ሕጋዊነት ያለው ፖለቲካ የማረጋገጥ አስተዋጽኦም ይኖረዋል። ጊዜያዊ የሰላም ስምምነቶች ወይም የኀይል እርምጃዎች ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንዳልቻሉ ያለፉት ዓመታት ማሳያዎች ናቸው። ሀገራዊ ምክክሩ ግን ስር የሰደዱ ችግሮችን በማንሳት ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት ያለው መፍትሔ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል። ሁሉም ወገን የተሳተፈበት ምክክር መከናወኑ ደግሞ የሚደረሱባቸው የጋራ ውሳኔዎች ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያደርጋል።
🇪🇹 በጥቅሉ ሀገራዊ ምክክር በራሱ ለሁሉም ጉዳዮች መፍትሔ ባይኾንም ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና የጦርነት ፖለቲካን ለመግታት ያለው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም። ኢትዮጵያ ከጠመንጃ ድምጽ ወጥታ በሀሳብ የበላይነት የምትመራበት ሰላማዊ ፖለቲካ እንዲተገበር የሁሉም ኢትዮጵያዊ በጎ ፍላጎት እና ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
#AMICO #NationalDialogue
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
