🇪🇹 የታላቁ ሀገራዊ ምክክር ጉዞ እና የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ 🤝

38

 

ኢትዮጵያ በታሪኳ ተደርጎ የማይታወቅ፣ በስፋቱ እና በጥልቀቱ ትልቅ የሀሳብ ልዕልና የሚነግስበት ታላቅ ሀገራዊ ምክክር እያደረገች ትገኛለች። በዚህም ከጫፍ እስከ ጫፍ የተውጣጡ፣ በኅብረ ቀለም የደመቁ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

​በተለይም ለዘመናት የዘለቁ የሀገሪቱ ችግሮች እና ቁርሾዎች የሚፈቱት፣ በልጆቿ ታፍራ እና ተከብራ የኖረች ሀገር የምትገነባው እና ለቀጣይ ትውልድም የተሻለች ሀገር ማስረከብ የሚቻለው በጽናት፣ በትጋት እና በመተጋገዝ ፈተናዎችን ማለፍ ሲቻል ነው።

ለዚህም ችግሮችን በንግግር እና በመደማመጥ መፍታት ወሳኝ መንገድ ነው። ይህን ችግሮችን በንግግር የመፍታት ባሕል ለማሳደግ ኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ሰንቃ ጉዞዋን ጀምራለች፤ የታለመውን እና የታቀደውንም ዕውን ለማድረግ እየተጋች ነው።

“አይሳካም” የሚሉ አሉባልታ ወሬዎች ቢነዙም ሀገሪቱ ለወሬ ቦታ የማትሰጥ እና ለተግባር የቆረጠች በመኾኗ ታፍራ እና ተከብራ ትቀጥላለች። የመረዳዳት ባሕልን በማሳደግም በተለያዩ ውበቶች አምራ እና ደምቃ ለሁሉም የጋራ የምትኾን ሀገር ትኖራለች።

​በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ካሳሁን አበራ ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እና መፃኢ ዕድል ለመወሰን እጅግ ሰፊ ዕድሎችን የሰነቀ ነው ይላሉ።

​መምህሩ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ውስጥ በርካታ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን አሳልፋለች። ሀገሪቱ ከቀድሞ ገናናነቷ ወጣ ብላ የሕዝቦች የመከፋፈል እና የልዩነት አዝማሚያዎች ጎልተው እንደታዩባት አንስተዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ እነዚህን የቆዩ ቁስሎች በውይይት እና በንግግር በመፍታት የላላውን ማኅበራዊ ትስስር ለማደስ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ይገልጻሉ።

​የጠላት ሴራዎች ኢትዮጵያን ለማጥፋት ቢሠሩም ይህ ሥራቸው ግን ሊሠምር አልቻለም፤ ልጆቿ ታላቂቷን ኢትዮጵያ እንደገና ለመገንባት እና የተከፋፈሉ ሕዝቦችን በአንድነት ለማስተሳሰር የሚያስችለውን ታሪካዊውን ሀገራዊ ምክክር ይዘው ብቅ ማለታቸውን ነው የገለጹት።

​ምክክሩም አብሮነትን ማጠናከር፤ በነጣጣይ ትርክቶች የተለያዩ ሕዝቦችን አንድ በማድረግ አብሮነትን እና መተማመን ያነግሳል ተብሎ እንደታመነበትም አስረድተዋል።

በተለይም የጋራ እና ገዢ ትርክት በመገንባት “ለኔ” ከማለት ይልቅ “ለእኛ” የሚል አስተሳሰብን በማስረጽ በጋራ ሀገር የመገንባት እሴት ያዳብራል ብለዋል።

የመደማመጥ እና የመነጋገር ባሕልን በማጎልበት የሀሳብ ልዕልና እንዲነግስ ያደርጋል። በምክክሩ ሂደት ማንም የበላይ ወይም የበታች ሳይኖር በሃሳብ የበላይነት የሚመራ ፍትሐዊ ሥርዓት እንዲዘረጋ ያግዛል ነው ያሉት።

በሀገሪቱ በሚከናወኑ ተግባራት ሁሉ የሀገሪቱን መጥፋት የሚመኙ ሁሉ በሴራዎች ጠልፎ ለመጣል እንደሚነሱ ያነሱት መምህሩ እስካሁንም ያጋጠሟትን ሴራዎች ሁሉ በጽናት እና በትጋት አልፋለች ነገም ትቀጥላለች ነው ያሉት። ኢትዮጵያውያን አዲስ ታሪክ መሥራት የተለመደ ተግባራቸው እንደኾነም በመጠቆም።

​ማኅበረሰቡ ከአሉባልታ እና ከሀሰተኛ ወሬዎች በመውጣት ትክክለኛውን የምክክር ሂደት እና የተወካዮቹን ድምጽ ብቻ ማዳመጥ እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት።

​ሕዝቡ የአሸባሪዎችን እና የሴረኞችን የውሸት ትርክት በመቃወም ምክክሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ እና አዲስ ታሪክ እንዲጻፍ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

ሀገሪቱ በፈተናዎች ውስጥ ሁሉ ፀንታ ማለፏን ያስታወሱት መምህሩ ይህ ሀገራዊ ምክክርም በስኬት
በመጠናቀቅ የነገዋን ጽኑ ሀገር ይገነባል ነው ያሉት።

#AMICO #NationalDialogue #የጋራትርክት #ኢትዮጵያ

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም

በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሀገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ ቅራኔዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መሠረት ይጥላል”
Next articleከጠመንጃ ፖለቲካ ወደ ምክክር ባሕል የሚደረግ የፖለቲካ ሽግግር 🤝