
የኢትዮጵያን የወደፊት የፖለቲካ ጉዞ የሚቃኝና ሀገርን በጋራ መክክር ለመገንባት ያለመ ታሪካዊ መድረክ ላይ የተሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ሀገራዊ ምክክሩ የነበሩ የፖለቲካ ቅራኔዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ትልቅ መሠረት እንደሚጥል ገልጸዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ተስፋሁን አለምነህ (ከአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ) እንደተናገሩት፣ ፓርቲያቸው ሲታገልላቸው የነበሩ መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በአጀንዳነት መያዛቸውን ገልጸዋል። ቀደም ሲል የነበሩት የቅራኔ መፍቻ መንገዶች አውዳሚ እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ተስፋሁን፣ ይህ መድረክ ሀገርን ከጦርነትና ከግጭት አዙሪት በማላቀቅ ለቀጣዩ ትውልድ ሰላማዊ ኢትዮጵያን ለማስረከብ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተመካካሪ የሆኑት አቶ የሱፍ ኢብራሒም በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ የአሁኑንና የቀጣዩን ትውልድ የሚያስተሳስር ጠንካራ መሠረት እንደሚጥል ገልጸው፣ አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት የሰለጠነ ባህልን ለማስረፅ የሚደረገውን ጥረት ማድነቃቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ባቀረበው አካታች ጥሪ መሠረት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳዎቻቸውን ይዘው በምክክሩ በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
#ኢትዮጵያ #ሀገራዊምክክር #የፖለቲካፓርቲዎች #ሰላም #Ethiopia #NationalDialogue
