🚗 በቴክኖሎጂ የተደገፈውን አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳና ዲጂታል የምዝገባ ሥርዓት በክልሉ ለመተግበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

6

 

የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) በአማራ ክልል የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን፣ የመንገድ ደኅንነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የትራንስፖርት ስምሪት እና ቁጥጥርን ውጤታማ ለማድረግ ያለመው በቴክኖሎጂ የተደገፈ አዲስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ እና የተቀናጀ የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓት ትግበራ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

🔹የአዲሱ ቴክኖሎጂ እና ሰሌዳ በመላ ሀገሪቱ ተመሳሳይ የኾነ ኅብረብሔራዊ መለያ ያለው በመኾኑ በክልሎች እና በዞኖች መካከል ወጥ አሠራር እንዲኖር ያስችላል ብለዋል። በካሜራ በቀላሉ መረጃዎችን ማንበብ የሚያስችል የፊደል እና ቁጥር አቀማመጥ፣ ባርኮድ፣ ኪው አር ኮድ ፣ የሰሌዳ ቺፕስ እና የመስታወት ላይ አር.ኤፍ.አይ.ዲ ቴክኖሎጂዎችን ያካተተ መኾኑን ገልጸዋል። ይህም ሀሰተኛ ሰሌዳ መሥራት እና ማጭበርበርን ሙሉ በሙሉ ያስቀራል ነው ያሉት።

ከነባሩ የማንዋል አሠራር በመውጣት ከብሔራዊ ዲጂታል የመረጃ ቋት ጋር የተሳሰረ በመኾኑ የወንጀል ምርመራን፣ የትራፊክ አሥተዳደርን እና የመንግሥት ገቢ አሠባሠብን ያሻሽላልም ነው ያሉት። አንድ ተሽከርካሪ አንዴ ሰሌዳ ከተሰጠው በኋላ እስከሚያረጅ ድረስ አብሮት የሚቆይ በመኾኑ ባለቤቱ ቢቀየር እንኳ ተጨማሪ ወጪ አያስወጣምም ብለዋል።

⚠️ አሠራሩ በጥንቃቄ እና በደረጃ እንደሚከናወን የገለጹት ኀላፊው አዲሱ ሰሌዳ በቅድሚያ የሚሰጠው አዲስ ለሚገቡ ተሽከርካሪዎች ብቻ መኾኑን ተናግረዋል። ነባር ሰሌዳዎችን በቀጥታ የመቀየር ሥራ አሁን ላይ እንደማይከናወንም ገልጸዋል። በየደረጃው በሚገኙ ቢሮዎች ተከማችተው የሚገኙ ያልተሰራጩ ነባር ሰሌዳዎች በሙሉ ወደ ክልሉ ቋት ገቢ ይደረጋሉም ብለዋል። እነዚህ ሳይሠበሠቡ አዲሱን ሰሌዳ ማሰራጨት በጥብቅ የተከለከለ መኾኑንም አመላክተዋል።
የተሽከርካሪ ባለቤቶች የተሽከርካሪ ባለቤትነት ማረጋገጫ፣ የሞተር እና የቻንሲ ቁጥር ትክክለኛነት፣ የቴክኒክ ብቃት ምርመራ ማሟላት እና አስፈላጊ ሰነዶችን ስካን አድርገው ወደ ሲስተሙ ማስገባት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል። ሥራውም በተዋረድ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች እንደሚተገበር አመላክተዋል። በቴክኖሎጂ የተደገፈው አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ እና ዲጂታል የምዝገባ ሥርዓት በክልሉ ለመተግበር በቂ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።

🤝በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የትራንስፖርት አገልግሎት እና ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ አሰፋ አዲስ መመሪያው ላለፉት ሦሥት ዓመታት በፌዴራል ደረጃ ሲዘጋጅ የቆየ እና የብዙ ባለድርሻ አካላትን ዕውቀት ያካተተ መኾኑን ተናግረዋል። አሠራሩ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በሙከራ ደረጃ ላይ የሚገኝ መኾኑንም ገልጸዋል። የሚስተዋሉ ግድፈቶችም ማሻሻያ ተደርጎባቸው ወደ ክልሎች ይወርዳል ብለዋል።

🧕የሥልጠናው ተሳታፊ አሚናት ጀማል ደግሞ አዲሱ አሠራር ከአዲስ አበባ ሰሌዳ የመጠበቅን እንግልት እንደሚያስቀር እና አጠቃላይ የመረጃ ልውውጥን በማቃለል አገልግሎቱን የተቀላጠፈ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። ሥልጠናውን መነሻ በማድረግም ወደ ሥራ ለመግባት እየተዘጋጁ መኾኑንም ጠቁመዋል።

#አሚኮ # #Transport #Ethiopia

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም

✍️ በሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“የስማርት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ግንባታ ለዛሬው ትውልድ ብቻ ሳይኾን ለነገውም ትውልድ ትልቅ አሻራ ነው” ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Next article“ሀገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ ቅራኔዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መሠረት ይጥላል”