
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከሰዎች ለሰዎች ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመኾን በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አያት ጣፎ አካባቢ የስማርት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐግብርን አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ሚሊዮን ማቴዎስ በከተማዋ የተጀመረው የስማርት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተያዘውን ብቁ የሰው ኀይል የማፍራት ራዕይ እውን የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ብቁ እና ተወዳዳሪ ሠልጣኞችን ለማፍራት በከተማዋ ከሚገኙት ከ14 የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች በተጨማሪ ግንባታው የተጀመረው የስማርት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ለሠልጣኞች የተሻለ ዕድልን ይዞ እንደመጣም ገልጸዋል።
የሰዎች ለሰዎች ግብረሰናይ ድርጅት የቦርድ ሠብሣቢ ሰባስቲያን ብራንደስ በበኩላቸው በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በመተባበር ዘጠነኛውን የስማርት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በጋራ ለመገንባት በመዘጋጀታችን ደስታ ተሠምቶናል ነው ያሉት።
ይህንን የስማርት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ፕሮጀክትም በተቀመጠለት ጊዜ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ለማስገባት እንሠራለንም ብለዋል።
በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማ አሥተዳደሩ ትውልድን በመገንባት እና የሙያ ባለቤት በማድረግ ረገድ ሰፊ ሥራ እየሠራ መኾኑን ጠቅሰው በከተማ አሥተዳደሩ የምንሠራው ፕሮጀክት ለዛሬ ትውልድ ብቻ ሳይኾን ለነገውም ትውልድ ትልቅ አሻራ ነው ብለዋል።
የሰዎች ለሰዎች ግብረሰናይ ድርጅት እየሠራ ያለው ሥራ ትልቅ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ይህ በአይነቱ ለየት ያለ የስማርት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ለሀገራችንም ኾነ ለከተማችን ትልቅ ዕድልን ይዞ የመጣ በመኾኑ አስፈላጊውን እገዛ እና ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ ገልጸዋል።
ኮሌጁ በውስጡ ዲጂታል ቤተ-መጽሐፍት፣ የቴክኖሎጂ ወርክሾፖች፣ መማሪያ ቁሳቁሶች፣ የአሥተዳደር ክፍሎች፣ የአረንጓዴ ልማት እና የስፖርት ሜዳዎችን ከልዩ ልዩ የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች ጋር አጣምሮ እንደሚይዝ ተነግሯል።
#አሚኮ #SmartPolytechnic #YouthEmpowerment
#አዲስ_አበባ፡ ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ፦ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
