
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መኾኑን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በሚያወጣቸው መግለጫዎች እያሳወቀ ይገኛል።
በምክክር ጉባኤው ሂደት ላይ አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ ወጣት ተሳታፊዎች የምክክር ጉባኤው ለኢትዮጵያ ወሳኝ ምዕራፍ መኾኑን እንደተገነዘቡ ተናግረዋል።
ምክክሩ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ እና ሁሉንም የሚወክሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተመካከሩበት በመኾኑ ተሳትፎው እና ሂደቱ ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ መኾኑን ነው የገለጹት። ልዩነቶቻችን እና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዕድል ፈጥሯልም ነው ያሉት።
ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል መመካከር ያለበት ለልዩነት ሳይኾን ለችግሮች መፍትሔ ለማምጣት መኾን አለበት ብለዋል። የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን በሂደት በመወያየት እና በመነጋገር ለችግሮች እልባት ለመስጠት መድረኩ ክፍት መኾኑን ጠቅሰዋል።
ማንኛውም የምክክሩ ተሳታፊ ጥላቻን አስወግዶ እና ከስሜታዊነት ወጥቶ በተሻለ መንገድ ተመካክሮ ለችግሮች መፍትሔ ለማስቀመጥ እየተመካከረ መኾኑንም ነው የጠቀሱት።
ሀገራዊ ምክክሩ ከዚህ በፊት ያልተለመደ ነገር ነው ብለዋል። ሀገራዊ ምክክር እና ውይይት በዚህ ዘመን መጀመሩም ደስተኛ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
ለዚህ ትውልድ ችግሮችን በምክክር እና በውይይት የሚፈታበትን ሂደትን እንደሚፈጥር እና ምክክርን ባሕሏ ያደረገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚጠቅምም ነው ያነሱት።
#አሚኮ #NationalDialogue #PeaceEthiopia 🕊️🇪🇹
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
