🌾🚜 በአማራ ክልል ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል።

10

 

ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚከናወኑ ቁልፍ ተግባራት መካከል የግብዓት አቅርቦት በወቅቱ እና በፍትሐዊነት ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ማድረግ አንዱ ነው። ይህንን እውን ለማድረግ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ለ2018/19 የመኸር እርሻ 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ አቅዶ እየሠራ ይገኛል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ የሺጥላ ፈቃዴ በ2018/19 የምርት ዘመን 945 ሺህ 961 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ መረጃው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 525 ሺህ 678 ኩንታል ለዞኑ ቀርቧል ብለዋል።

​በምርት ዘመኑ ከ641 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የገለጹት ኀላፊው ከዚህ ከ28 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ግብ መቀመጡን አንስተዋል። ይህንን ግብ ለማሳካትም ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

​ውቅታዊ ሁኔታዎች ቀደም ሲል የግብዓት አቅርቦት ውስንነት ፈጥረው እንደነበር አንስተዋል። አሁን ላይ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግሮች በመፈታታቸው አጠቃላይ የግብዓት ሥርጭቱ 89 በመቶ ለወረዳዎች ተዳራሽ ኾኗል ብለዋል። ለአርሶ አደሮችም በፍትሐዊነት እየተሠራጨ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
​
ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የባለሙያ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ በተያዘው የመኸር እርሻ በክልሉ 5 ነጥብ 58 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች እንደሚሸፈን ገልጸዋል። ከዚህም 205 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

​በምርት ዘመኑ ለማቅረብ ከታቀደው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 5 ሚሊዮን 580 ሺህ 272 ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል ነው ያሉት።

​በተወሰኑ ዞኖች በተለይም በደቡብ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች አጋጥሞ የነበረውን የመዘግየት ችግር በመቅረፍ አሁን ላይ በቂ መጠን ያለው የማዳበሪያ አቅርቦት እየቀረበላቸው ይገኛል፤ ከእነዚህ ውጭ በሌሎች ዞኖችም ግብዓቱን በወቅቱ እና በፍትሐዊነት ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

በተለይም ቀድመው ለሚዘሩ ዘሮች ግብዓት ለአርሶ አደሮች በወቅቱ ተደራሽ መደረጉን ጠቁመዋል። ሥራው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

አሁን ላይ የግብዓት አቅርቦት ችግር የለም ያሉት ኅላፊው ለአርሶ አደሮች በወቅቱ እና በፍትሐዊነት ተደራሽ ለማድረግ ከግብርና ሚኒስቴር ጀምሮ እስከ ታች ድረስ ክትትል ተደርጓል ብለዋል።

ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ማዳበሪያውን የማጓጓዝ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ሕገወጥ የግብዓት ዝውውርን ለመከላከል በግብረ-ኀይል በቅንጅት እየተሠራ ነው፤ በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የተገኙ አካላት ላይም ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መኾኑን ነው የገለጹት። አርሶ አደሮችም ከግል ነጋዴዎች ማዳበሪያ እየተገዛ ሲያጋጥማቸው በአቅራቢያቸው ለሚገኙ የሕግ አካላት በማሳወቅ የበኩላቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።

​መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ በማድረግ አርሶ አደሮችን እየደገፈ በመኾኑ ሕገወጥ የግብዓት ዝውውር የሚያደርጉ አካላት በሕግ ተጠያቂ እንዲኾኑ የማኅበረሰቡ ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል። በቀጣይም ቁጥጥር እና ክትትሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።

#አሚኮ #የመኸርእርሻ #FertilizerSupply #የአማራ_ክልል

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም

በሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሀገር የምትገነባው በሁላችንም ተሳትፎ ነው” የምክክር ጉባኤ ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች
Next articleከልዩነት ወደ መፍትሔ፤ የወጣቶች ተሳትፎ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ላይ