
በዓለም ሙዚቃ ታሪክ ተወዳጅ የኾነው አካል ጉዳተኛ ድምጻዊ እና የዘፈን ግጥም ደራሲ ስቲቪ ዋንደር “አንድ ሰው የዓይኖቹን ብርሃን ስላጣ ብቻ ራዕይ የለውም ማለት አይደለም” ሲል አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ሰው ስኬታማ መኾንን እንደሚፈልጉ ሰለ አካል ጉዳተኞች ራዕይ ይናገራል።
ሌላኛው በግጥሞቹ እና በአነቃቂ ንግግሮቹ የሚታወቀው አሜሪካዊው አካል ጉዳተኛ ሮበርት ሄንሰል “በችሎታዬ እወቁኝ እንጂ በአካል ጉዳተኝነቴ አይደለም” በማለት አካል ጉዳተኞች በችሎታቸው እንዲመዘኑ እና እንዲታወቁ ድምጽ ኾኗል።
ይህንን ሃሳብ ስለ አካል ጉዳተኝነት ጉዳት ለማንሳት አይደለም ያነሳነው ይልቁንስ አካል ጉዳተኞች ለማኅበረሰቡ እና ለሀገር የበኩላቸውን መወጣት እንደሚችሉ ለማሳየት ነው።
በተፈጥሮ ወይንም በሰው ሠራሽ አደጋ የአካል ጉዳት ይከሰታል። የኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ መለስ ብሎ ለሚቃኘው አካል እምብዛም ለአካል ጉዳተኛ ትኩረት ሲሰጥ አይስተዋልም ነበር።
እስከ ቅርብ ጊዜ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት አካል ጉዳተኞች ተሳታፊ ሲኾኑ ማየት አልተለመደም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከአካል ጉዳተኞች ንቁ ተሳትፎ እና መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች በሰጠው ትኩረት ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ተሳታፊ እና ወሳኝ ሲኾኑ እየተመለከትን ነው።
ይህንን የሚያረጋግጠው ደግሞ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ተሳትፏቸው ነው። በርካታ አካል ጉዳተኞች ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አሳታፊ ባደረገው በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ጉባኤ ተሳታፊ ኾነዋል።
በምክክሩ ተሳታፊ የኾኑት ዘሪቱ ማሞ ምክክሩ የአካል ጉዳተኞች ድምጽ እንዲሰማ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል። አካል ጉዳተኞች ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን ይወጣሉ ነው ያሉት።
አካል ጉዳተኞች ከጓዳ እንዲወጡ፤ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ፤ በሥራቸው ውጤታማ እንዲኾኑ ምክክሩ ትልቅ ዕድልን ይፈጥራል ብለዋል።
ሌላኛዋ ተሳታፊ ጀሚላ አብደላ ምክክሩ ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ መኾኑን ተናግረዋል። ሁሉንም ዜጋ ያካተተች ሀገር አሸናፊ እንደምትኾንም ነው ያነሱት።
ሌላኛዋ የምክክሩ ተሳታፊ ኤደን ጌታቸው ምክክሩ አካል ጉዳተኞች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ፤ በቀጣይ ይበልጥ በሀገራቸው ጉዳይ ተሳታፊ እንዲኾኑ ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት።
ጦርነት አውዳሚ በመኾኑ ሰላም፤ ፍቅር እና አንድነትን እንዲሁም መመካከርን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ነው ያሉት።
#አሚኮ #ሀገራዊምክክር #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_17_2018 ዓ_ም
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
