🚨 ሕገወጡ ሕወሃት የጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ፈረስ ነው።

6

 

ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ዛሬም የሰላም ጥሪዎችን በመግፋት ዳግም ወደ ጦርነት እያመራ ነው። ቡድኑ ከተፈጠረበት የጥላቻ እና የጠላትነት ፖለቲካ ራሱን አላቆ ወደ መደበኛ እና ሰላማዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመሸጋገር ባለመቻሉ የውጭ ኅይሎች ኢትዮጵያን እንዲያፈርሱ እና ራሱንም በሕይወት ለማቆየት እየሠራ ይገኛል።

👉የውጭ ኅይሎች ጥምረት እና የቡድኑ ታሪካዊ አቋም

የተቀናሽ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ማኅበር ፕሬዝዳንት ፲ አለቃ ደጀኔ ሸዋረጋ ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን የኢትዮጵያን ጠንክሮ መውጣት ከማይፈልጉ ጸረ ኢትዮጵያ የውጭ ኅይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር ሀገሪቱን ወደ ማያባራ ጦርነት እና ትርምስ ለማስገባት እየሠራ ነው ብለዋል።

ሕገ ወጥ ቡድኑ “አስተማማኝ የውጭ ኅይል አጋር አለን” ማለቱ ይህንን ዕቅድ በይፋ ያሳየበት እንደኾነም ጠቅሰዋል።

የሕገወጡ ሕወሃት ሀገር የማፍረስ ተግባር አዲስ እንዳልኾነ የጦር መኮነኑ ማሳያዎችን በመጠቆም አስረድተዋል። ድርጅቱ ገና በ1969 ዓ.ም ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ወራሪውን ኅይል ደግፎ መግለጫ ማውጣቱ ሀገር አፍራሽነቱ የቆየ ፍላጎቱ እንደኾነ የሚያሳይ መኾኑን አስረድተዋል።

👉የመከላከያ ሠራዊት ዝግጁነት እና የመንግሥት አቋም

ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን የውጭ ኅይሎችን ቢያሰልፍም ራሱን በሪፎርም አዘጋጅቶ በተሻለ ቁመና ላይ በሚገኘው የሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንደማያሳድር በልበ ሙሉነት ተናግረዋል።

የመንግሥቱ የበዛ ትዕግስት ለሕዝብ ከማሰብ እና በወታደራዊ ሳይንስ መርህ ላይ የተመሠረተ ነው ብለው እንደሚያስቡም ጠቁመዋል።

👉አማራ ክልልን የጦርነት ቀጣና ማድረግ

፲ አለቃ ደጀኔ ቡድኑ ውድመቱን በአማራ ክልል ለማድረግ በክልሉ ያሉ ታጣቂዎችን በመሳሪያ፣ በፖለቲካ እና በፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

እንደ ፲ አለቃ ደጀኔ ሸዋረጋ ቡድኑ:-

👉እንደ 1982 እና 83 ዓ.ም በአማራ ሕዝብ እና ወጣት ትከሻ ላይ ተራምዶ ሥልጣን መያዝን ቀዳሚ ዓላማው አድርጎ እየተንፈራገጠ መኾኑን ተናግረዋል።

👉 የጦርነቱን አድማስ በማስፋት፣ መሠረተ ልማቶችን በማውደም እና ሕዝቡን በማፈናቀል የከሰረ የፖለቲካ ፍላጎቱን ማካካሻ ማድረግንም ሌላኛ ዕቅዱ አድርጓል።

👉የፕሪቶሪያን ስምምነት መጣስ

ቡድኑ ተፈናቃዮች አልተመለሱም የሚለውን ሰበብ ችግር ለመፍጠር ለመጫወቻ ካርድነት እየተጠቀመ ነው፤ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት በምርጫ ቦርድ ሕልውናውን ያጣ፣ ከትግራይ ሕዝብ የተነጠለ እና በጥቂት ቤተሰባዊ ኀይሎች ብቻ የተደራጀ “የግል ማኅበር ኾኗል” ብለዋል።

የሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ክልልን ወርቅ በሕገ ወጥ መንገድ በመሸጥ፣ የትግራይን ወጣቶች ለሱዳን በመሸጥ እና ለውትድርና በመመልመል በሚያገኘው የሕገ ወጥ ንግድ ገንዘብ እየተንቀሳቀሰ መኾኑን ገልጸዋል።

👉ቡድኑን ለማክሰም ምን ይደረግ?

የተቀናሽ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ማኅበር ፕሬዝዳንት ፲ አለቃ ደጀኔ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ከመንግሥት ጋር በሀሳብ አለመስማማት አንድነገር ኾኖ ከሀገር አፍራሽ ኅይሎች ጋር መቆም ግን በታሪክም የሚያስወቅስ ተግባር ነው ብለዋል። ከእንግዲህ አይነት ተግባር መውጣት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ከጠመንጃ አፈሙዝ የሚመጣ ሰላም እና ልማት የለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ የተጀመረውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በመጠቀም ሀሳብን ወደ ገበያ ማውጣት ብቸኛው አማራጭ ሊኾን እንደሚገባ አስቦ መሥራት ከሁሉም እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ሕገ ወጡ ሕወሃት በአሁኑ ወቅት ብቻዬን አልሞትም በሚል የትግራይን ሕዝብ እና ወጣት ይዞ ለመጥፋት እየተንቀሳቀሰ መኾኑንም ጠቁመዋል። የትግራይ ሕዝብም በቃ በማለት ድርጅቱን መቃወም ይኖርበታል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት በመቀሌ ከተማ ወጣቶች እምቢተኝነታቸውን ፊሽካ በመንፋት እና ሾልከው ከአካባቢው በመውጣት ተቃውሞ እያሰሙ ቢኾንም የትግራይ እና የአማራ ሕዝብን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊ ከዚህ በኋላ ጦርነት አንፈልግም በሚል እምቢተኝነታቸውን በመግለጽ የቡድኑን ግብዓተ መሬት ማፋጠን ይገባቸዋል ብለዋል።

#አሚኮ #ሕገወጡየሕወሃትቡድን #በቃህሊባልይገባዋል

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“የክረምት በጎ ፈቃድ እርስ በእርስ የምንተጋገዝበት እና በጎነትን የምናሳይበት ነው” ዶክተር መቅደስ ዳባ
Next article“ሀገር የምትገነባው በሁላችንም ተሳትፎ ነው” የምክክር ጉባኤ ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች