
የጤና ሚኒስቴር ከቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ጋር በመተባበር የክረምት በጎ ፈቃድ ነጻ የሕክምና እና የምክር አገልግሎት መርሐ ግብር አስጀምረዋል። በበጎ ፈቃድ ተግባሩ ከ 30 በላይ የሕክምና ተቋማት ተሳታፊ ይኾናሉ ተብሏል።
የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ዶክተር አብረሃም እሸቴ ሆስፒታሉ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን ለመወጣት የክረምት በጎ ፈቃድ ነጻ የሕክምና እና የምክር አገልግሎት ይሠጣል ብለዋል፡፡
በዚህ መርሐግብር ከ120 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታሰቡንም ገልጸዋል። ነጻ ሕክምናው ከፍተኛ የዲያግኖስቲክ አገልግሎት እና ቀዶ ሕክምናን የሚያካትት መኾኑንም ተናግረዋል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ እርስ በእርስ የምንተጋገዝበት እና በጎነትን የምናሳይበት ነው ብለዋል።
የሕክምና ባለሙያዎችም በዚህ ተሳትፏቸው ከሁልጊዜው በተለየ ሕዝባቸውን በቀናነት ለማገልገል ዕድል ይሰጣቸዋል ነው ያሉት፡፡
የሚሰጠው ነጻ የሕክምና እና የምክር አገልግሎት የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል እና ሥራዎችን ቀድሞ ለማከናወን እንደሚረዳ ተናግረዋል። ይህን ጥሩ አጋጣሚ ኅብረተሰቡም ጤናውን ለመከታተል ያስችለዋል ነው ያሉት።
በዚህ ክረምት አገልግሎቱን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ20 ሚሊዮን ሰዎች ለመስጠት መታቀዱንም አመላክተዋል።
የግልም ኾነ የመንግሥት የጤና ተቋማት ይህን በጎ ተግባር ለመደገፍ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
#አሚኮ #የክረምትበጎፈቃድ #ነፃሕክምና
#አዲስ_አበባ፡ ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ: ሰላማዊት ነጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
