
በከተማ ልማት ዘርፍ ሥር የተደራጁ የአማራ ክልል ሥራ እና ክሕሎት ቢሮ እና የአማራ የብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ ባለሥልጣን በ2018 ዓ.ም ክሕሎትን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የባለሙያዎችን ብቃት በምዘና የማረጋገጥ ቅንጅታዊ አፈጻጸም እና የክረምት ወራት የ90 ቀናት እቅድ እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራት ላይ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የአማራ ክልል ሥራ እና ክሕሎት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አማረ ዓለሙ ቢሮው አምሥት ዋና ዋና የትኩረት መስኮች እንዳሉት አንስተዋል። እነዚህን ተግባራት ለማሳለጥ አዳዲስ እሳቤዎች ተግባራዊ ተደርገዋል ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 58 ሚሊዮን በላይ ሥራ አጥ ወጣቶችን በመመዝገብ፤ የአመለካከት እና የክሕሎት ሥልጠና በመስጠት እና ከ74 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዝችን በማደራጀት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
ከነዚህ ውስጥም ከ986 ሺህ በላይ ቋሚ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው መኾናቸውን ገልጸዋል። በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ከ149 ሺህ በላይ የሚኾኑ ዜጎች ሠልጥነው እና ተመዝነው መላካቸውንም ጠቅሰዋል።
ለኢንተርፕራይዞች በሀገር ውስጥ ገበያ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር እና በውጭ ሀገር ደግሞ ከ1 ሚሊዮን 329 ሺህ ዶላር በላይ የገበያ ትስስር በመፍጠር ውጤታማ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል። የተዘዋዋሪ፣ የመደበኛ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶችን ጨምሮ 10 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ብድር ለኢንተርፕራይዞች መቅረቡንም ጠቅሰዋል።
በጥቅሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም መስኮች ውጤታማ ተግባራት ሲከናወኑ የከተማ ዘርፍ ተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር የሚበረታታ እንደነበር ነው የተናገሩት።
በበጀት ዓመቱ የጸጥታ ችግር ተደራሽነት ላይ ችግር መፍጠሩ፣ የዋጋ ግሽፈት እና ተግባርን በባለቤትነት ከመፈጸም አኳያ ክፍተቶች እንደነበሩ አንስተዋል።
የአማራ የብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ ባለሥልጣን ዳይሬክተር ተስፋዬ የሺዋስ ባለሥልጣኑ ሥራ ከጀመረበት ዓመት ጀምሮ የበርካታ ዜጎችን የሙያ ብቃት በማረጋገጥ ለኢንዱስትሪው የራሱን ድርሻ እያበረከተ መኾኑን ተናግረዋል።
ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመቱ የሙያ ብቃት ምዘና መስጫ ማዕከላት በማደስ እና የሙያ ብቃት መዛኞችን በማፍራት ውጤታማ ሥራ ሠርቷል ነው ያሉት።
ለሥራ ስምሪት የብቃት ማስረጃ ወሳኝ በመኾኑ ዜጎች ወደ ምዘና እየገቡ መኾናቸውን ጠቅሰዋል። በበጀት ዓመቱም 224 ሺህ በላይ ሠራተኞች ተመዝነው 70 በመቶው በቅተው ኢንዱስትሪውን እየተቀላቀሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ከምዝገባ ጀምሮ እስከ ምዘና ሰርቲፊኬት ያለውን ሂደት ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል። በሙያ ብቃት ምዘና የጥራት ጉዳይ አሁንም ያልተቀረፈ ችግር መኾኑን ጠቅሰዋል። በቀጣይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
በየዘርፉ ለተመዘገበው ውጤት የክተማ ዘርፍ ቅንጅታዊ አሠራር አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን በመግለጫው ተነስቷል። በተጀመረው መንገድ ተጠናክሮ ከቀጠለ የክልሉ ሕዝብ በዘርፎቹ የሚፈልገውን ውጤት የሚያገኝበት ዕድል እንደሚፈጠርም ተነስቷል።
የሥራ ኀላፊዎቹ የክረምት ወራት የእረፍት ሳይኾኑ የሥራ ጊዜያት ናቸው በሚል በከተማ ዘርፍ ሥር በተደራጁ ተቋማት የ90 ቀናት እቅድ ማዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል። የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች፣ የጸረ ሙስና ሥራዎች እና መሰል ተግባራት ታቅደው እየተሠሩ መኾናቸውን ነው በመግለጫቸው የተናገሩት።
#የከተማዘርፍ_ቅንጅታዊአሠራር
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
