
የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ ውይይት አካሂዷል።
የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ ተሾመ አግማስ በ2018 በጀት ዓመት ተቋሙ በአካባቢ ጥበቃ፤ በደን ጥበቃ፤ በዱር እንስሳት ጠብቃ እና ልማት ላይ በትኩረት መሥራቱን ገልጸዋል።
በአካባቢ ጥበቃ ከ6 ሺህ በላይ የልማት ፕሮጀክቶች የይሁንታ ሰርቲፊኬትን በመስጠት ወደ ተግባር እንዲገቡ ተደርጓል ነው ያሉት። በደን ልማት 210 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱንም ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ የወፍ ዋሻን ከጥብቅ ደን ወደ ብሔራዊ ፖርክ እንዲያድግ ተሠርቷል ነው ያሉት። የነበረው ጸጥታ ችግር ሥራዎችን በይበልጥ ለማከናወን እንቅፋት ፈጥሮ እንደነበር ጠቁመዋል።
ውኃማ አካላትን የመጠበቅ እና የማልማት ሥራ መከናወኑንም ገልጸዋል። በጣና ሐይቅ 2 ሺህ 800 ሄክታር መሬት ላይ የእምቦጭን አረም የማስወገድ እና ወደ ሐይቁ የእምቦጭ አረም እንዳይገባ የማልማት ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት። የከተሞችን ጽዳት እና ውበት ለመጠበቅ ከሌሎች ተቋማት ጋር በተቀናጀ መንገድ ተሠርቷል።
በ2019 በጀት ዓመት ክፍተቶችን በመለየት እና ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ይሠራል ብለዋል። ቅንጅታዊ አሠራር ተግባራዊ ይደረጋል ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አካባቢ ጥበቃ ጽዳት እና ውበት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጽጌሬዳ አበበ በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፤ ብክለትን በመቆጣጠር እና የአረንጓዴ አሻራ ልማት ላይ በትኩረት ተሠርቷል ብለዋል።
በቆሻሻ እና ፍሳሽ አወጋገድ ላይ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ በማከናወን እና በአግባቡ በማያስወግዱ ላይ እርምጃ በመወሰድ አካባቢን ንጹሕ ለማድረግ ተሠርቷል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ የአካባቢውን ንጽሕና በአግባቡ በመጠበቅ ለከተማዋ ልማት የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አካባቢ እና ደን ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ካሳዬ ስመኝ በዞኑ በርካታ ወረዳዎች ጣና ሐይቅን የሚያዋስኑ በመኾናቸው ሐይቁን ከእምቦጭ አረም የማጽዳት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
እምቦጭ የተወገደባቸውን አካባቢዎች የተለያዩ እፅዋቶችን በመትከል መልሶ ለማልማት ተሠርቷልም ብለዋል።
#አሚኮ #አካባቢጥበቃ #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_17_2018 ዓ_ም
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
