
የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሸከርካሪዎች ታርጋ መቀየርን አስመልክቶ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የማስፈጸሚያ መሠረታዊ አቅጣጫዎች ሥልጠና እየሠጠ ነው።
የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) በአዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ የተሽከርካሪ ምዝገባን በቴክኖሎጅ በማዘመን የመንገድ ደኅንነትን የማረጋገጥ፣ የትራንስፖርት ስምሪት፣ ቁጥጥርን እና የአገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማ የማድረግ ዓላማ መያዙን ተናግረዋል።
ለልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት ሥልጠና መስጠት አስፈላጊ ኾኖ ተገኝቷልም ብለዋል። በቀጣይም አተገባበሩ ላይ ከሠልጣኞች ትልቅ ኀላፊነት እንደሚጠበቅ ነው ያስገነዘቡት።
በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ክልሎች ላይ በተዋረድ ወጥ የኾነ የሰሌዳ ቁጥር እንዲኖር ለማድረግ የተሽከርካሪ ሰሌዳ መቀየር አስፈላጊ እንደኾነም ገልጸዋል። በሀገር እና በክልል ደረጃ የሚኖረው ፋይዳ ተመጋጋቢ እና ተመሳሳይነት ያለው እንደኾነም አንስተዋል።
አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ሲቀየር ዝም ብሎ ቁጥር የመቀየር ጉዳይ አይደለም ያሉት ኀላፊው በገንዘብ፣ በጉልበት እና በዕውቀት የተለፋበት ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው ብለዋል። በሀገሪቱ ወጥ የኾነ የሰሌዳ ቁጥር እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ ያለውን ሥራ በክልሉ ለመተግበር እንደ ክልል ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።
#አሚኮ #የሰሌዳቀየራ #TransportEthiopia #የአማራክልል #VehiclePlate
#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ፡- ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
