ሀገራዊ ምክክር በሂደቱ አሳታፊነትን እና አካታችነትን መርሁ አድርጎ ሠርቷል።

4

 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ አካላት በተገኙበት ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

የምክክር ጉባኤውም ሀገርን ሊያሻግሩ በሚችሉ የሕዝብ አጀንዳዎች ላይ ነው እየመከረ የሚገኘው።

የሠመራ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዲያቆን ዳንኤል ጌትነት ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ኮሚሽኑ ከቀበሌ ጀምሮ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሊወክሉ የሚችሉ አካላትን በመምረጥ በውይይት ሂደቱ ተሳታፊ እንዲኾኑ ማድረጉ ኹሉንም አካታች የኾነ ሥራ መሥራቱን ያመላክታል ብለዋል።

ከሀገር ሽማግሌ እስከ ሃይማኖት አባቶች፣ ከሴቶች እስከ አካል ጉዳተኞች፣ ከሲቪክ ማኅበራት እስከ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ የዲያስፖራ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና ከሌሎችም ማሳተፉ አካታች እና ኹሉንም ያማከለ እንዲኾን አስችሏል ነው ያሉት። ይህም ኮሚሽኑ ለሚሠራው ሥራ ግልጽነትን የፈጠረ መኾኑን አንስተዋል።

ምክክሮች በየደረጃው መደረጋቸው የከረሙ ችግሮች እና አሉ የሚባሉ ቁርሾዎች በአጀንዳነት ተይዘው ምክክር እንዲደረግባቸው ዕድል የፈጠረ መኾኑን ገልጸዋል።

በክልል ደረጃ በተካሄደው ጉባኤም ተሳታፊዎች በሀገር ደረጃ ለሚካሄደው ጉባኤ አጀንዳ የሚኾኑ ጉዳዮችን ተመካክረው መስጠታቸውን አስታውሰዋል።

ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ለቀጣይ ሀገራዊ አንድነት በመፍጠር እና ችግሮችን በመፍታት ሚናው ላቅ ያለ መኾኑን አስረድተዋል።

በሀገር ደረጃ ምክክር መካሄዱ የሚያስገኘውን ጥቅም ሲያብራሩ እንዳሉት፡-

👉 ብሔራዊ መግባባትን ያመጣል፣

👉በተለያዩ ጉዳዮች የነበረውን መለያየት እና አለመግባባቶችን ይፈታል፣

👉 ሕዝቡ ልዩነትን እንደ ጌጥ እንጂ እንደመለያያ እንዳይጠቀም ያስችላል፣

👉 በኹሉም ዘንድ መስማማት እና ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል፣

👉 የጋራ ትርክቶች ላይ መግባባትን ይፈጥራል፣

👉ሰላማዊ የትግል ባሕል እንዲዳብርም ያስችላል፣

👉 ሰላማዊ የፖለቲካ ባሕል እንዲዳብር እና እንዲያድግ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።

እንደሀገር “እኔ ነኝ የበላይ፤ እኔ ነኝ አሸናፊ”ከሚል የፖለቲካ አካሄድ በመውጣት በጋራ ሀገርን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ የሚያስችል ምክክር ይደረጋል ተብሎ ይታመናል ነው ያሉት።

“ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ ፈተናዎችን በድል የተሻገረች ሀገር ናት” ያሉት መምህሩ በተለይ ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ ከማስረከብ ይልቅ በትጥቅ ትግል ለመቀማት የሚደረግ አካሄድ ለሀገራዊ ፖለቲካ ምኅዳር መስፋት አይጠቅምም ነው ያሉት።

ችግሮች በአንድ ጊዜ እርግፍ ብለው ይቀረፋሉ ባይባልም በምክክር ሂደት ደረጃ በደረጃ ችግሮች እንደሚፈቱ ሕዝቡ ተስፋ ማድረግ ይገባዋል ነው ያሉት። የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የተጣለበትን ተስፋ በአግባቡ እንዲወጣም ኹሉም አካል የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

#አሚኮ #ሀገራዊ_ምክክር #NationalDialogue #ሰላምእናአንድነት #Ethiopia

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም

ዘጋቢ፡- ሰለሞን ስንታየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“የጋራ ተጠቃሚነታችን የሚረጋገጠው የሌሎችንም ሕመም መታመም ስንጀምር ነው”
Next articleበ2018 በጀት ዓመት 2 ሺህ 800 ሄክታር መሬት ከእምቦጭ አረም ጸድቷል።