
በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ግለሰባዊ እና ማኅበረሰባዊ ግጭቶችን በመከላከል እና በማስወገድ ማኅበረሰባዊ ሰላም እና አንድነትን የሚጠብቁበት ጥበብ እየተካሄደ ለሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ወሳኝ ልምድ የሚወሰድበት ነው።
የሀገር ሽማግሌዎች የተጣሉ ወገኖችን ለማስታረቅ በመጀመሪያ ጠበኞችን ፊት ለፊት ከማገናኘታቸው በፊት ሁሉንም ለየብቻ በማነጋገር እና ሀሳባቸውን በማዳመጥ ስሜታቸውን ያረግባሉ። እውነተኛ ፍላጎታቸው ምን እንደኾነም በውል ይረዳሉ።
ከዚያም ራሳቸውን ከስሜት እንዲያስወጡ፤ ሽማግሌ የሚላቸውን እንዲቀበሉ እና ልባቸውን ለዕርቅ እና ለይቅርታ ዝግጁ እንዲያደርጉም አደራ ይሰጧቸዋል። መቸም ሰው ከግጭት ይልቅ በሰላም መኖርን መሻቱ ተፈጥሯዊ ሥሪቱ ነውና ጠበኞቹም ለእርቅ እና ለይቅርታ ዝግጁ መኾናቸውን ያረጋግጣሉ።
በቀጥታ ወደ እርቅ ሥርዓቱም ይገባሉ። ሽማግሌዎቹም “አንተ ከዚህ ላይ ስተሃል፣ አንተም እዚያ ላይ አጥፍተሃል፤ አንተም ተው አንችም ተይ” በማለት የሁለቱን የጥፋት ሚዛን ያጣጥማሉ። የአንዱ ጥፋት የጎላ ቢኾንም እንኳን ፍጹም ንጹሕ እና ፍጹም በዳይ አድርጎ ከመፈረጅ ተቆጥበው ሁለቱም ጥፋተኛ መኾናቸውን እንዲያምኑ ያደርጋሉ።
ሁሉንም እኩል ዝቅ በማድረግ አሸናፊም ተሸናፊም እንዳይኖር በማድረግ የአንደኛው ወገን “ተበድያለሁ ለእኔ ካልተፈረደልኝ” የሚለውን ግትርነቱን እንዲተው ይልቁንስ ለይቅርታ እና ለሽማግሌዎቹ ክብር ሲሉ ይቅርታ እንዲጠያየቁ ይለምናሉ።
በመጨረሻም የሀገር ሽማግሌዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ክብርና ተሰሚነት ከፍተኛ ስለኾነ እርቁን ይቀበላሉ። ጠበኞቹ መሳሪያ አጋድመው፤ ድንጋይ በትከሻቸው ተሸክመው ይቅር ይባባላሉ። የእርቁ የደስ ደስ ይደገሳል በጋራ ማዕድ ይቆረሳል።
በዚህ መልኩ ሊፈስስ የነበረ ደም፤ ሊጠፋ የነበረ ሕይወት ተርፏል። ደም የተቃቡ ብዙ ጠበኞች፤ ሊበተን እና ሊሰደድ የነበረ ብዙ ቤተሰብም ድኗል። ሊተላለቁ ነው በሚል ወሬ የተበከለው አየር በሰላም ነፋስ ይሞላል።
እናም በመካሄድ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤም ከዚሁ የተቀዳ እንደመኾኑ የሀገር ሽማግሌዎቹ ብልሃት ዓይነት ልብ ከሁሉም ይፈልጋል።
ምክክሩ ቀጣይነት ያለው እንደመኾኑ ለሚቀመጡ መፍትሔዎች ተመካካሪዎች ልባቸውን ክፍት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ይታመናል።
የምክክሩ የመጨረሻ ግብ ኢትዮጵያን ከአለመግባባት እና ግጭት አፋትቶ ሰላም እና አንድነቷን ማስጠበቅ ነው። ስለኾነም ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የያዘው ትልቅ ግብ ተሳክቶ የተፈለገውን ዘላቂ ሰላም እንዲያመጣ ከተመካካሪዎችም ኾነ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወሳኝ እና መሠረታዊ ተግባራት ይጠበቃሉ።
ተመካካሪዎች ለተያዙ አጀንዳዎች የሚሰጡ መልሶች እና የሚቀመጡ መፍትሔዎች ጠቀሜታቸው ለሀገር ሰላም እና አንድነት መኾናቸውን ማሰብ ይኖርባቸዋል። “የእኔ ብቻ” ከሚል የራስን ፍላጎት ብቻ አግዝፎ ከማየት፤ የሌላውን ወገን ሕመም አለመታመም እና ከመሰል የቆዬ አጉል ልማዶች ራሳቸውን ማንጻት ይጠበቅባቸዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት አሕመድ ሁሴን የምክክር መድረኩ የራሳችንን አቋም የምናጸባርቅበት ብቻ ሳይኾን በሌሎች ጫማ ላይ ቆመን ስጋታቸውን የምንጋራበት መኾን አለበት ነው ያሉት። የሁላችንንም የጋራ ተጠቃሚነት የምናረጋግጠው እና እውነተኛ የሀገር ፍቅርም የሚለካው በዚህ መንገድ ነው ብለዋል። ይህ የእርስ በእርስ መተማመን ይገነባል፤ ዘላቂ ሰላምን ያረጋግጣል፤ ሕዝባችን እና ሀገራችን ከተጋላጭነት ያስወጣል ነው ያሉት።
በአጠቃላይ እውነተኛ ሰላም ከራስ ነው የሚጀምረው። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ለብሔራዊ ምክክሩ መሳካት የራሱን የሰላም አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል።
#አሚኮ #ሀገራዊ_ምክክር #NationalDialogue🇪🇹
#ባሕር_ዳር ሐምሌ17_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
