🗣️ ሀገራዊ ምክክሩን ከተዛቡ መረጃዎች መከላከል የሕልውና ጉዳይ ነው

10

 

ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ ልዩነቶችን ለማረቅ፣ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የሚካሄድ እጅግ ወሳኝ ሂደት ነው። ሂደቱ በሚካሄድበት ወቅት ኾን ተብለውም ኾነ በስህተት የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች እና የሀሰት ትርክቶች በምክክር ሂደቱ፣ በውጤቱ እና በተቀባይነቱ አደጋን ይደቅናሉ።

“በቀውስ ጊዜያት ሐሰተኛ መረጃ በሕዝብ አመለካከት ላይ ያለው ተጽዕኖ” በሚል የተጠናቀረው እና ‘ሪሰርች ጌት’ ድረ ገጽ ላይ የተጋራው ጥናታዊ ጽሑፍ የሐሰተኛ መረጃ መበራከት በመረጃ ምንጮች ታማኝነት ላይ ግራ መጋባትን እና ጥርጣሬን በመፍጠር ሕዝቡ በባለሥልጣናት፣ በባለሙያዎች እና በተቋማት ላይ ያለውን አመኔታ ሊሸረሽር እንደሚችል አትቷል።

ሐሰተኛ መረጃ የማኅበራዊ መከፋፈልን እና ልዩነቶችን በማባባስ አመኔታን ይበልጥ በማዳከም የቀውስ ምላሽ ጥረቶችን ውስብስብ እንደሚያደርግም አጽንኦት ሰጥቷል።

ሀገራዊ ምክክር ስኬታማ የሚባለው ከምክክሩ በኋላ የሚወጡት የጋራ ስምምነቶች በሕዝቡ ዘንድ አመኔታን አግኝተው ወደ ተግባር ሲለወጡ ነው። በዚህ ሂደት ግን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ ሚዲያዎች እና ከግጭት ትርፍን የሚፈልጉ አካላት የተሳሳቱ መረጃዎችን ሊረጩ ይችላሉ። የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንም ይህንን በማስታወቅ የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፏል።

“ምክክሩ የአንድን ወገን ፍላጎት ብቻ ለማስፈጸም የታለመ ነው” ወይም “አካታች አይደለም” የሚሉ የመሠረተ ቢስ መረጃዎች ስርጭት የፖለቲካ ተዋናዮች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን ከሂደቱ እንዲያገሉ ለማድረግ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ፍንጭ የሚሰጥ ነው።

እንደ ሀገራዊ ምክክር ባሉ ትልልቅ ሁነቶች ወቅት የሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎች መድረኩ ከሃሳብ ልውውጥ ወጥቶ የንትርክ እና የጥላቻ ንግግር ማስተጋቢያ እንዲኾን፣ አጀንዳዎች ከዋናው የሀገር ግንባታ እና የሰላም ጉዳይ ወጥተው ወደ ግጭት አባባሽነት እንዲያመሩ ሊያደርጉም ስለሚችሉ ጥንቃቄ ይሻል።

ለአብነት በኮሎምቢያ ከመንግሥት እና ከፋርክ አማጺያን ጋር ያደረገችውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ሕዝቡ በውጤቱ ላይ ድምጽ እንዲሰጥ በተደረገበት ወቅት በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ የተቀነባበሩ የሀሰት መረጃዎች ለምክክሩ ፈተና ደቅነው ነበር።

በየመን እ.ኤ.አ ከ2013 እስከ 2014 በተካሄደው ብሔራዊ የምክክር ጉባኤ ወቅትም የተለያዩ የፖለቲካ እና የሃይማኖት ቡድኖች ሚዲያን እና ማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም የየራሳቸውን የተዛቡ ትርክቶች ሲያሰራጩ ነበር። ይህ ድርጊት በተሳታፊዎች መካከል የነበረውን መተማመን ከማጥፋቱም በላይ ሕዝቡ በምክክሩ ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ አድርጓል። ሀገሪቱ ወደከፋ የእርስ በርስ ጦርነት እንድታመራ ከተጫወቱት ሚናዎች መካከል ዋነኛው የሀሰት መረጃዎች ስርጭት እና የሚዲያ ጽንፈኝነት ነው።

ሀገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲኾን እና ተቀባይነት ያለው ውጤት እንዲያመጣ የተሳሳቱ መረጃዎችን መከላከል የቅንጦት ሳይኾን የህልውና ጉዳይ መኾን ይኖርበታል። ይህንንም ለማድረግ የምክክር ኮሚሺኑ እና የሚመለከታቸው አካላት:-

👉 ወቅታዊ እና ትክክለኛ መረጃዎችን ለሕዝቡ በግልጽ ማድረስ፣
👉 ጠንካራ የመረጃ ማጣሪያ ሥርዓትን መዘርጋት

👉 የሕዝቡን የመረጃ አጠቃቀም ግንዛቤ ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል።

የተሳሳቱ መረጃዎች የሚፈጥሩትን ስጋት አስቀድሞ መገንዘብ እና መከላከል ሀገራዊ ምክክሩ የሰላም እና የእርቅ መሠረት እንዲኾን ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም ዜጎች በማኅበራዊ ሚዲያ ከሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎች እና አሉባልታዎች ራሳቸውን በመጠበቅ ሂደቱን በትዕግስት እንዲከታተሉ፣ መረጃዎችን ከኮሚሽኑ ይፋዊ ምንጮች እና ታማኝ ሚዲያዎች ብቻ በመውሰድ ለታሪካዊው ምክክር ስኬት የጋራ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል።

#አሚኮ #AMICO #ሀገራዊ_ምክክር

#ባሕር_ዳር ሐምሌ16/2018 ዓ.ም

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“አካባቢን መንከባከብ ለትውልድ የሚሰጥ ሕይወት ነው” አቶ ይትባረክ አወቀ