በአማራ ክልል ስምንት ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎቻቸውን አሳልፈዋል።

34

 

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ውጤታቸውን ከቀጣይ ሰኞ ጀምሮ ማወቅ እንደሚችሉ የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሰጡት መግለጫ የ2018 የትምህርት ዘመን የማለፍያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ20 ሺህ ብልጫ አለው ብለዋል።

በ2018 የትምህርት ዘመን ከተፈተኑ 550 ሺህ ተማሪዎች መካከል 70 ሺህ 544 ተማሪዎች አልፈዋል ነው ያሉት። ውጤት ካስመዘገቡት ውስጥ 16 ነጥብ 5 በመቶ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ናቸው። 8 ነጥብ 33 በመቶ ደግሞ ከማኅበራዊ ሳይንስ መኾናቸውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል።

በክልል ደረጃ ሁሉም መሻሻል ማሳየታቸው የገለጹት ሚኒስትሩ አዲስ አበባ 32 ነጥብ 3 በመቶ በማሳለፍ የተሻለ ኾኗል። አማራ ክልል 15 ነጥብ 56 በመቶ፣ ኦሮሚያ ክልል 10 ነጥብ 53 በመቶ አሳልፈዋል ብለዋል።

ምንም ተማሪ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ቀንሷል ያሉት ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት ከነበረው 1 ሺህ 232 ትምህርት ቤቶች፣ በዚህ ዓመት ቁጥራቸው ቀንሶ 565 ብቻ ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ ሳያሳልፉ ቀርተዋል ነው ያሉት። በአማራ ክልል ስምንት ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ አሳልፈዋል ተብሏል።

በውጤት ደረጃ 583 ውጤት በማምጣት በአማራ ክልል ሁለተኛው ከፍተኛ ውጤት ኾኖ ተመዝግቧል። በዓመቱ ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 62 በመቶ የሚኾኑት በኦንላይን ፈተናውን መውሰዳቸውን አስታውቀዋል። በውጤት ደረጃም የተሻሉ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ ዓመት ሙሉ ለሙሉ በኦንላይን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ሀብቴ ተሻገር

#አዲስ_አበባ #ነሐሴ_16_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ኢትዮጵያ ልዩ ሀገር ናት፣ በዓለም ክፍል ያሉ ሁሉ እንዲጎበኟት እንመክራለን” የውጭ ሀገር ጎብኝዎች