“አካባቢን መንከባከብ ለትውልድ የሚሰጥ ሕይወት ነው” አቶ ይትባረክ አወቀ

12

 

የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የዓለም የአካባቢ ቀን በዓል የማጠቃለያ ኘሮግራምን የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት አካሂዷል። የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለ ሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ በአሁኑ ወቅት የአየር ንብረት ለውጥ የብዝሃ ሕይወት መመናመን እና የአካባቢ ብክለት ዓለም አቀፍ ቀውሶች መኾናቸው ገልጸዋል። የፕላስቲክ ብክለት በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱ በወንዞች፣ በአፈር እና በሰዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ነው ያሉት።

ይህን ለመከላከል እንደ ሀገር እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች ለውጦች እየተመዘገቡ ነው ብለዋል።
በተለይም በኮሪደሪ ልማት እና በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለውጥ እየመጣ መኾኑን ነው የገለጹት።

በቀጣይም የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል በቅንጅት መሠራት እንዳለበት ነው የተናገሩት። የዕለት ከዕለት ተግባር በማድርግም ዛሬ መሥራት ለነገ መሠረት ማስቀመጥ ይገባል ብለዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድሩ ልዩ አማካሪ ይትባረክ አወቀ ከለውጡ መንግሥት በኋላ ከተለዩ የፌዴራል ዕቅዶች መካከል ጽዱ ኢትዮጵያን ለትውልድ የማውረስ ዕቅድ አንዱ በመኾኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሕዝብ ንቅናቄ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

አካባቢን ማጽዳት፣ ማስዋብ፣ ለሰዎች የተመቸ ማድረግ፣ ከተሞችን መግለጥ፣ ውበታቸውን ማጉላት እና ለቱሪስት መስህብነት ትልቅ መዳረሻ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት።

ከፍተኛ ተጽዕኖ የነበረውን የፕላስቲክ ምርት እና ተረፈ ምርት የመቆጣጠር እና ማስወገድ ደንቦችን እና አዋጆችን በማውጣት ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል ነው ያሉት። በክልሉም ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ በርካታ የአካባቢ ጥበቃ እና የመቆጣጣር ሥራ መከናወኑን ነው የተናገሩት።

በዚህም ለሰው ልጆች የተመቼ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ያሉት አቶ ይትባረክ “አካባቢን መከባከብ ለትውልድ የሚሰጥ ሕይወት ነው” ብለዋል።

የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ በልስቲ ፈጠነ መድረኩ በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራት እና ያለፉትን ዓመታት ሥራዎች በአዲስ መልክ በመገምገም፣ ከተሞችን ጽዱ እና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ ያለመ ውይይት ነው ብለዋል። በፌዴራል ደረጃ በተጀመረው የ”የጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ” ንቅናቄ ማዕቀፍ ውስጥ እስከ 423 ሺህ ኪሎ ግራም ፕላስቲክ በክልሉ ተሰብስቧል ነው ያሉት።

በሁሉም አካባቢዎች የሰዎችን አስተሳሰብ በመቀየር ንጽህናን እንደ ባሕል ለማዳበር በቅንጅት ይሠራልም ብለዋል።

የሰሜን ሽዋ ዞን አካባቢ ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበበ ታደግ አካባቢን ከጉዳት ለመታደግ በተለይም የፕላስቲክ ብክለትን ለመከላከል የሚያስችል ጥብቅ ሕግ ወጥቶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

የልማት ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ መሠረታዊ መኾኑንም ተናግረዋል ።

#አሚኮ #አረንጓዴ_አሻራ #ኢትዮጵያ
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_16_2018 ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጹን ያሰማበት ታሪካዊ ዕድል
Next article🗣️ ሀገራዊ ምክክሩን ከተዛቡ መረጃዎች መከላከል የሕልውና ጉዳይ ነው