የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጹን ያሰማበት ታሪካዊ ዕድል

11

 

የካቲት/2014 ዓ.ም በኢትዮጵያዊያን ጥያቄ መሠረት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት፤ የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል በጋራ ለመወሰን 11 ኮሚሽነሮችን የያዘ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቋመ።

ኮሚሽኑ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት በምክክር የሀገራቸውን ችግር መቅረፍ የቻሉ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮን አጥንቷል። ኮሚሽኑ በመላ ሀገሪቱ እና በውጭ ሀገር የሚገኙ ዜጎችን ጥያቄ በመሠብሠብ የጋራ አጀንዳን ማዋቀርም ችሏል።

በአካል ጥያቄዎችን ከሕዝብ ከመቀበል ባሻገር በበይነ መረብ እና በውጭ ሀገራት በመገኘት የዲያስፖራውን ማኅበረሰብ ጥያቄም ማካተት ችሏል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መሐመድ ድሪር ሀገራዊ ምክክሩ የሊህቃን ብቻ ሳይኾን ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍሎች የተካተቱበት መኾኑን ተናግረዋል።

የምክክር ኮሚሽኑን ሂደት ተዓማኒ፤ ቅቡል እና አካታች ለማድረግ ተሠርቷል ነው ያሉት። ከሕዝብ የተሠበሠቡ ጥያቄዎችን በአጀንዳ በመለየት ውጤታማ ምክክር እንዲፈጸም መሠራቱንም ተናግረዋል።

የ4ሺህ ሰዎች ብዝኀነት እና የአጀንዳዎቹ ስፋት ሀገራዊ ምክክሩን የተለዬ እንደሚያደርገው አንሥተዋል። ሁሉም ማኅበረሰብ ቋንቋውን ተጠቅሞ ድምጹን አሠምቷል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር መሳካት ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የሰላም እና መረጋጋት ምንጭ መኾኑንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከውጭ የመጣ ሰው ችግሩን እንደሚፈታለት አያምንም በራሱ መንገድ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት መርጧል ነው ያሉት።

ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲኾን በሰከነ፤ በመከባበር እና ዴሞክራሲያዊ በኾነ መንገድ ሕዝቡ የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም ገልጸዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረ ሥላሴ በአጀንዳ ልየታው አርሶ አደሮች፤ ሴቶች፤ አረጋውያን፤ ወጣቶች፤ አካል ጉዳተኞች፤ ተፈናቃዮች፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥያቄያቸውን ማሰማት ችለዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ነጻነት ድምጹን ያሰማበት ታሪካዊ ዕድል መኾኑንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመመካከር ለሀገራቸው የጋራ ርዕይ የሚፈጥሩበት መኾኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ አጀንዳዎቹ ከሕዝብ ፍላጎት፤ ተስፋ እና ስጋት የተቀዱ ናቸው ብለዋል። ለኢትዮጵያ በሕዝብ ድምጽ የተመሠረተ ታማኝ፤ አካታች፤ ግልጽ እና ሳይንሳዊ ምክክር ማድረግ ፍቱን መድኀኒት መኾኑን ተናግረዋል።

የሀገርን እጣ ፈንታ የሚወስኑ፤ በመሠረታዊ የሀገር ግንባታ ጉዳዮች ላይ መግባባት፤ ለዘመናት ሲያጋጩ የነበሩ ጉዳዮች ላይ የጋራ መፍትሄ በማስቀመጥ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ማስፈን ይጠበቃል ነው ያሉት።

ከጠበበ የቡድን እና የግል ፍላጎት በመውጣት ለሀገር ሰላም እና ለቀጣዩ ትውልድ ዕጣ ፈንታ በሆደ ሰፊነት እና በሀቀኝነት መምከር ይገባል ብለዋል።

#አሚኮ #ምክክርኮሚሽን #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

✍️ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleለሁሉም የሚያዋጣው ሰላማዊ መንገድ ነው።
Next article“አካባቢን መንከባከብ ለትውልድ የሚሰጥ ሕይወት ነው” አቶ ይትባረክ አወቀ