ለሁሉም የሚያዋጣው ሰላማዊ መንገድ ነው።

16

 

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ የክልሉን የሰላም ሁኔታ አብራርተዋል።

በማብራሪያቸውም ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል። የክልሉን ሕዝብ ሕይወትም አመሠቃቅሏል ነው ያሉት።

ኅብረተሰቡ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ ተስተጓጉሏል፤ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲገታ ኾኗል፤ ለአርሶ አደሮች ግብዓት በወቅቱ እንዳይደርስ፣ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታቸው እንዲስተጓጎሉ ምክንያት መኾኑን አብራርተዋል።

ጽንፈኛ ኀይሉ የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች አስመልሳለሁ የሚል መነሻ ቢኖረውም በተጨባጭ በተቃርኖ መቆሙን ነው የገለጹት። በአንጻሩ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን በማወሳሰብ ለማዳፈን እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ለአብነትም ወልቃይትን እና ራያን አሳልፎ ለመስጠት ከሕወሃት ጋር እየሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል።⚠️

🕊️ክልሉን ወደ ሰላም ለመመለስ በተደረገው ጥረት ከፍተኛ መሻሻል እየመጣ መኾኑን አብራርተዋል። ኅብረተሰቡም የታጣቂ ኀይሉን እኩይ ዓላማ በመረዳት ግንዛቤው ተለውጧል ነው ያሉት።

የክልሉን ሰላም በራስ አቅም ለመጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ ተቋም እየተገነባ እንደሚገኝም አመላክተዋል። የሚሊሻ፣ የአድማ መከላከል እና የፖሊስ ኀይልን በማሠልጠን እና በማጠናከር ሰፊ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።

እንደ ኀላፊው ማብራሪያ የታጠቁ ኀይሎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ መንግሥት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን አቅርቧል። የሰላም አማራጭን ተቀብለው የሚገቡ ኀይሎችን ለማስተናገድ የሚያስችል መመሪያም ተዘጋጅቷል።

🔄ወደ ሰላም የተመለሱት የተሃድሶ ሥልጠና እየተሰጣቸው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እየተደረጉ ነው። የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ቀደመ የሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ፣ የመሥሪያ እና የመሸጫ ቦታዎች እና የፋይናንስ ድጋፎች እንዲመቻቹ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የሰላም እጦት ምን ያሕል ዋጋ እንደሚያስከፍል ከክልሉ ሕዝብ በላይ የተረዳው የለም ያሉት ኀላፊው የሰላም ዋጋው ትልቅ እና የሁሉም መሠረት መኾኑ ገብቶታል ነው ያሉት። በዚህ ምክንያት ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም ሰላምን ለማምጣት በሚደረገው ሁሉን ዓቀፍ ጥረት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

🤝ለሁሉም የሚያዋጣው ሰላማዊ መንገድ በመኾኑ ሁሉም የታጠቁ ኀይሎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ የክልሉ መንግሥት ጽኑ አቋም መኾኑን ተናግረዋል።

የውጭ ጠላቶችን ጣልቃ ገብነት ለመከላከልም ጠንካራ ውስጣዊ አቅም እየተገነባ መኾኑን ጠቁመዋል። በዚህም “ክልሉን ለሕገወጥ ቡድን የማይመች እናደርጋለን” ብለዋል።

💡የክልሉ መንግሥት “ለግጭት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፤ እርስ በርስ ከመግጠም ከድህነት ጋር እንግጠም፤ ከጦርነት ይልቅ ለልማት ዋጋ እንክፈል፤ ክልሉን በጋራ እናልማ” የሚል አቋም እንዳለውም ጠቁመዋል።

#አሚኮ #አማራክልል #ሰላም #AmharaRegion #Peace #Ethiopia 🇪🇹

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ ከ215 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኘ።
Next articleየኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጹን ያሰማበት ታሪካዊ ዕድል