ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ ከ215 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኘ።

16

 

ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ይፋ ያደረጉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበጀት ዓመቱ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይም የኔትወርክ ተደራሽነት እና ዘመናዊነትን ለማሻሻል በበጀት ዓመቱ 603 አዲስ የሞባይል ኔትወርክ ጣቢያዎች ተገንብተው ወደ አገልግሎት ማስገባት ተችሏል። እንደሀገርም የሞባይል ጣቢያዎች ብዛት 10 ሺህ 613 ደርሷል ብለዋል።

195 የገጠር ሞባይል ጣቢያዎችን በመገንባት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የገጠር ማኅበረሰብን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ያሉት ሥራ አሥፈፃሚዋ በበጀት ዓመቱ ፈጣን የ5G አገልግሎትን 33 ከተሞች እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም እንደሀገር የደንበኞች ቁጥርን 90 ነጥብ 1 ሚሊዮን ያደረሰ ሲኾን ይህም የዕቅዱን 101 ነጥብ 7 በመቶ ማድረስ ችሏል። ይህም ባለፈው ዓመት ከነበረው 8 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ዋና ሥራ አሥፈጻሚዋ ተናግረዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 215 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል ነው ያሉት። ይህ ገቢ የተገኘው ከድምጽ ጥሪ፣ ከኢንተርኔት አገልግሎት፣ ከመሠረተ ልማት ማጋራት፣ ከቴሌኮም ቁሳቁስ ሽያጭ እና ከሌሎች የዲጂታል ፋይናንስ ምንጮች ሲኾን ገቢው ከባለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር 33 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል።

የቴሌኮም አገልግሎት አሰጣጡን ከማስፋት እና ጥራቱን ከማሳደግ አኳያ ከፍተኛ ዕድገት መመዝገቡን እና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረትም ትርጉም ያለው ሥራ መሠራቱን አንስተዋል።

በመላ ሀገሪቱ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የፈጣን ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ምቹ ምኅዳር ተፈጥሯል ነው ያሉት።

ኢትዮ ቴሌኮም ቴሌብርን ጨምሮ በዲጂታል ፋይናንሻል አገልግሎት እና ስማርት ሲቲን በመገንባት በከተሞች የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያን የማስፋፋት ሥራን እየሠራ እንደሚገኝም ተጠቅሷል።

#አሚኮ #EthioTelecom #DigitalEthiopia🇪🇹

#አዲስ_አበባ፡ ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

ዘጋቢ: ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“የምክክር ጉባኤው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው” ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
Next articleለሁሉም የሚያዋጣው ሰላማዊ መንገድ ነው።