
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የምክክር ጉባኤውን ሂደት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው የምክክር ጉባኤው ተሳታፊዎች በቡድን በቡድን እየኾኑ ሀሳብ የማመንጨት እና የማጠናቀር ሥራ ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በቡድን ተከፋፍለው መወያየታቸው በደንብ ተቀራርበው እና ተዋውቀው የተሰጧቸውን አጀንዳዎች በትክክል ማብላላት እንዲችሉ ያደርጋል ነው ያሉት።
ተከባብረው፣ ተነጋግረው እና ተደማምጠው ወደ ሀሳብ ማጠናከር ሂደት እንዲገቡ የማድረግ ውጤታማ ሂደት መድረጉንም ገልጸዋል።
ዛሬ ደግሞ ግብዓት ሊኾናቸው የሚችሉ መረጃዎችን የሚያካፍሉ በሀገር ላይ በተለያዩ ዘርፎች ብዙ ዕውቀት ያከማቹ ምሁራን በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ሀሳቦችን እንዳቀረቡላቸው ነው የገለጹት። በቀረቡ ሀሳቦች ላይም ጥያቄዎችን አቅርበው ምላሽ ይሰጥቷቸዋል ነው ያሉት። ሂደቱ በሚቀጥለው ሳምንትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሂደቱ የሚስተካከሉ ጉዳዮች በትኩረት ይፈታሉም ነው ያሉት። የሕክምና፣ የጸጥታ፣ የትራንስፖርት እና ሌሎች ተቋማት የተሰጣቸውን ኀላፊነት በአግባቡ እየተወጡ መኾናቸውንም ጠቁመዋል።
የሚዲያ ተቋማት ተደራሽነት ለምክክሩ ወሳኝ መኾኑን ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ ሂደቱን እየተከታተሉ ለሕዝቡ ማድረስ ተገቢ ነው ብለዋል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለቀቁ አንዳንድ የተሳሳቱ መረጃዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
#አሚኮ #ሀገራዊምክክር
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_16_2018 ዓ_ም
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
