ሀገር በምክክር ትጸናለች!

22

 

የተመካከሩ ሀገር አጽንተዋል፤ ነጻነትን ጠብቀዋል፤ ሉዓላዊነትን አስከብረዋል፤ ኪሣራን አስቀርተዋል፤ ቂም እና በቀልን አርቀዋል።

የተመካከሩ ግጭትን አድርቀዋል፤ ጦርነትን ታሪክ አድርገዋል፤ የተመካከሩ ሀገራቸውን አጠንክረዋል፤ ጽኑ መሠረት ላይ አቁመዋል። ሀገር በምክክር ትዋባለች፤ በምክክርም ታድጋለች።

የተመካከሩ ፈተናዎችን ተሻግረዋል፤ የተሻለ ሀገር ገንብተዋል። ለልጆቻቸው ሰላም የሰፈነባት፤ አንድነት የደረጀባት፤ ምጣኔ ሃብት ያደገባት፤ ፍትሕ እና ርትእ የተረጋገጠባት ሀገር አውርሰዋል።

ኢትዮጵያውያን ለዘለመናት የጸናች ሀገራቸውን የበለጠ ለማጽናት፤ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ከዳር እስከ ዳር ተጠራርተው በአንድ አዳራሽ ተሰባስበው እየመከሩ ነው። ይህ ምክክር ኢትዮጵያውያን ወርቃማ ታሪክ የሚጽፉበት፤ ሰላምን የሚያጸኑበት እና በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት የሚደርሱበት ነው።

አምባሳደር ብሩክ መኮንን ብሔራዊ ምክክር፤ ለተሻለ ነገ የጥፋት አዙሪትን መስበር በሚል ርእስ በጻፉት ጽሑፍ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኢትዮጵያን ዘመናዊ ታሪክ ሲፈታተኑ የቆዩትን ስር የሰደዱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የብሔር ልዩነቶችን ለመፍታት የተወጠነ እጅግ አስፈላጊ ጥረት ነው ብለውታል።

በብዙ ብሔር፣ በፖለቲካዊ ውብስብነቷ እና በረጅም ታሪኳ ለምትታወቀው ኢትዮጵያ ውይይት አስፈላጊ ብቻ አይደለም፤ ግዴታ ነው እንጂ። ሀገራዊ ምክክር የተንሰራፉ ልዩነቶችን መፍታት የሚጀምር መሳሪያ ነው። በብሔር፣ በፖለቲካ እና በክልል አጥር የተከለሉ ሀሳቦችን በማውጣት መረዳዳትን እና ትብብርን ያጎለብታል፤ የታሪክ ቁስሎችን ለማከም ይረዳል፤ ለረጅም ጊዜ ለቆዩ ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት ዕድል ይሰጣል ነው የሚሉት።

ሀገራዊ ምክክር ኢትዮጵያውያን በጋራ የወደፊት ራዕይ ዙሪያ እንዲሰባሰቡ የሚያደርግ መኾኑንም ገልጸዋል። ሂደቱ ግን ፈጣን ውጤት ለማስገኘት የታለመ ሳይኾን ጊዜን፣ ጽናትን እና የሕዝቡን የጋራ ፍላጎት ወይም ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኢትዮጵያ በአስቸኳይ የምትፈልገውን ሰፊ እና አሳታፊ የምክክር መድረክ ለማሳደግ መቋቋሙን የሚያነሱት አምባሳደሩ ይህም እንዲሁ ለተፈጠሩ ሁኔታዎች ምላሽ ለመስጠት ብቻ የተደረገ እንቅስቃሴ ሳይኾን የኢትዮጵያ ፈተናዎች በግጭት ወይም በመከፋፈል ሊፈቱ እንደማይችሉ በመገንዘብ አስቀድሞ የተወሰደ እርምጃ ነበር ይላሉ።

ኢትዮጵያ እውነተኛ ውይይቶችን ለማመቻቸት የተጋ ተቋም ያስፈልጋት ነበር፤ ለዚህም ነው የተቋቋመው ብለዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተወጣጡ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ተስፋቸውን፣ ስጋታቸውን እና የወደፊት ሕልማቸውን ያንጸባረቁበት እና የሚያንጸባርቁበት ተቋም ነው።

ሙሉ ነጻነቱን ጠብቆ የሚንቀሳቀሰው ኮሚሽኑ በውይይቶቹ ውስጥ የተለያዩ አመለካከቶችን ለማካተት በትጋት ሢሠራ ቆይቷል። የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ድምፅ ሙሉ በሙሉ ለማንጸባረቅ ያለመ አሳታፊ የምክክር ሂደትን ለማጎልበት ማኅበረሰቦችን፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን፤ የክልል መሪዎችን እና የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎችን አሳትፏል።

የኮሚሽኑ ሚና ውሳኔዎችን መጫን ሳይኾን ትርጉም ላላቸው እና እርስ በርስ መከባበር ለተሞላባቸው ውይይቶች ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው፤ ይሄንንም አድርጓል ብለዋል። ኮሚሽኑ ሰፊ እና ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ ውክልና እንዲኖር የተቀናጀ ጥረት አድርጓል ነው የሚሉት።

​ኮሚሽኑ ለገለልተኝነት እና ላለማደላት የጸና ቁርጠኝነት አለው። በነጻነት የሚንቀሳቀስ ነው፤ ዋና አላማውም ሁሉም ድምጾች በነጻነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መድረክ መፍጠር ነው። የመጨረሻው ግብ ኢትዮጵያ ከመከፋፈል ወጥታ በትብብር፣ በጋራ ክብር እና ለሰላም በሚደረግ የጋራ ቁርጠኝነት ወደተቀረጸ የጋራ መፃኢ ዕድል እንድትሸጋገር ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሂደቱ የጸጥታ ችግር እና ሌሎች ፈተናዎች ቢገጥሙትም ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በሂደቱ ውስጥ ለማሳተፍ የያዘውን ጽኑ አቋም ሳያላላ በቁርጠኝነት ሠርቷል። ዕርቅ እና ሰላም ግንባታ በአንድ ጀምበር የሚኾኑ አይደሉም የሚሉት አምባሳደሩ ረጅም ጊዜን የሚጠይቁ ጥረቶች ናቸው ብለዋል።

ምክክሩ ዠ የተሻለች የወደፊት ሀገርን ለመገንባት የሚደረግ አስፈላጊ እርምጃ ነው። የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ድምጹ የሚሰማበት፣ ዋጋ የሚያገኝበት እና ተወካይነት ያለው ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ በዕርቅ ፍለጋ ጉዞዋ ውስጥ ብቻዋን አይደለችም የሚሉት አምባሳደሩ በዓለም ዙሪያ እንደ ደቡብ አፍሪካ እና ኮሎምቢያ ያሉ ሀገራት ምክክር ክፍፍሎችን ለማሸነፍ እና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ኃይለኛ መሣሪያ መኾን እንደሚችል አሳይተዋል ብለዋል። ከእነዚህ አብነቶች የሚገኘው በጣም አስፈላጊው ትምህርት የአካታችነት ዋጋ እንደኾነም ገልጸዋል። ለዚያም ነው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አካታችነትን እና አሳታፊነትን መርሁ አድርጎ የሠራው።

ምክክር ፈጣን መፍትሔ አይደለም፤ ጊዜን፣ እምነትን እና አስቸጋሪ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ፈቃደኛ መኾንን ይጠይቃል የሚሉት አምባሳደሩ በምክክር ትዕግሥት መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ ወደ ጋራ መግባባት የምታደርገውን ጉዞ ከልብ ሊቀበሉት ይገባል፤ ምክንያቱም ጉዳዩ ከሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ጋር የተያያዘ እና ዋጋው በጣም ከፍተኛ በመኾኑ ነው ይላሉ።

የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዓላማ የትኛውም ያህል የብሔር ወይም የፖለቲካ ልዩነት ቢኖር፣ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን አካታች፣ ፍትሐዊ እና ትክክለኛ የኾነ የመልካም አሥተዳደር ሥርዓት ማንበር ነው። ይህ የምክክር መድረክ ለሀገሪቱ ተደራራቢ ፈተናዎች ሁሉ እንደ ተአምረኛ ፈውስ የሚታይ ባይኾንም አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ወሳኝ እና አስፈላጊ እርምጃ ነው ብለውታል።

እንደ የመልካም አሥተዳደር ሥርዓት፤ የሀብት ክፍፍል እና የፖለቲካ ውክልና ያሉ ቁልፍ ጉዳዮችን በውይይት በመፍታት፣ ምክክሩ እያንዳንዱ ዜጋ የማደግ እና የመበልጽግ ዕድል የሚያገኝበትን መሠረት ይጥላል፤ የኢትዮጵያ ትልቅ ምኞት እና ሕልምም ይኸው ነው ይላሉ። ማንኛውም ዜጋ የብሔርም ኾነ የክልል ማንነቱ ሳይገድበው፣ በሰላም አብሮ የሚኖርባት እና አብሮ የሚበለጽግባት ሀገር መፍጠር የኮሚሽኑ ዓላማ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፤ ብሔራዊ የምክክር መድረኩም የውስጥ ፈተናዎችን አልፎ የበለጠ አሳታፊ እና ዴሞክራሲያዊት የኾነች ሀገር ለመገንባት ታሪካዊ ዕድልን ይዟል። ይሄን እዠዕድል መጠቀም ደግሞ ከኢትዮጵያውያን ይጠበቃል።

#አሚኮ ​#ሀገራዊ_ምክክር
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_16_2018 ዓ_ም

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ደሜ የአንዲት እናት ሕይዎት ማዳኑ ሲነገረኝ ከፍዬ ያሳከምኩ ያህል ደስታ ተሰምቶኛል”🩸🤱✨
Next article“የምክክር ጉባኤው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው” ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ