“ደሜ የአንዲት እናት ሕይዎት ማዳኑ ሲነገረኝ ከፍዬ ያሳከምኩ ያህል ደስታ ተሰምቶኛል”🩸🤱✨

17

 

የአማራ ክልል የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ሠራተኞች እና መሪዎች የደም ልገሳ መርሐ ግብር አካሂደዋል።

የአማራ ክልል የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ምክትል ኀላፊ ሞላ ትዕዛዙ ዛሬ የተከናወነው የደም ልገሳ መርሐ ግብር የዘንድሮውን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ አካል መኾኑን ተናግረዋል። አገልግሎቱ ባለፉት ዓመታትም በየክረምቱ ተመሳሳይ የደም ልገሳ ተግባራትን በስኬት ማከናወኑን አስታውሰዋል።

በሕይዎት አድን መርሐ ግብሩ ላይ የተቋሙ ሠራተኞች በከፍተኛ ተነሳሽነት እና በሙሉ ፈቃደኝነት እየተሳተፉ ይገኛሉ ብለዋል።

የባሕር ዳር ደም ባንክ የጤና ባለሙያው መላክ ውዴ በደም ባንኮቻችን ያለው የደም ክምችት ተስፋ ሰጪ መሻሻሎችን እያሳየ ቢመጣም አሁንም የሁሉንም ታካሚዎች ሕይዎት ለመታደግ የሚያስችል በቂ አቅም ላይ አልደረሰም ነው ያሉት። በተለይም በክረምቱ ወቅት ትምህርት ቤቶች የሚዘጉበት እና የዝናብ ጊዜ በመኾኑ ከፍተኛ የኾነ የደም እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቁመዋል።

መስፈርቱን የሚያሟሉ ዜጎች ሁሉ ደም በመለገስ የሰብዓዊነት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ለጋሾች በማንኛውም ሰዓት ወደ ደም ባንክ በመምጣት ወይም ደም ባንኩ በተለያዩ አካባቢዎች በሚያሰማራቸው ተንቀሳቃሽ የደም መሰብሰቢያ ጣቢያዎች ላይ በመገኘት መለገስ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ደም መለገስ የሌላውን ሰው ሕይዎት ከመታደግ ባለፈ ነገ ለራስም ኾነ ለቤተሰብ አባላት ደም ቢያስፈልግ ችግር እንዳይፈጠር የሚያግዝ እንደኾነ የተናገሩት ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው ዘመኑ ወርቁ ናቸው። ማንኛውም ሰው ደም እንዲለግስ ጥሪ አስተላልፈዋል። በቀጣይም የባለሙያዎችን ምክር በመከተል የደም ልገሳቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ሌላኛዋ ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሰብለ ሽመልስ ባለፈው ዓመት “የለገስኩት ደም የአንዲት እናት ሕይወት ማዳኑ ሲነገረኝ ከፍዬ ያሳከምኩ ያህል ደስታ ነው የተሰማኝ” ብለዋል። አሁንም ሁሉም ወገኖች የዘመቻ እንቅስቃሴዎችን ሳይጠብቁ ደም በመለገስ የበኩላቸውን ሕይዎት የማዳን አስተዋጿቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የሲቪል እና ቤተሰም ምዝገባ አገልግሎት ያስጀመረው የደም ልገሳ የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ በዋናው መሥሪያ ቤት ብቻ ሳይወሰን በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖች እና ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል።

#አሚኮ #ደም_ልገሳ
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_16_2018 ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🇪🇹ኢትዮጵያ ያላትን አትሰጥም፤ የሌሎችንም አትነካም
Next articleሀገር በምክክር ትጸናለች!