🇪🇹ኢትዮጵያ ያላትን አትሰጥም፤ የሌሎችንም አትነካም

13

 

ለዘመናት በቋጥኞች መካከል እየጎረፈ የተፋሰሱን ሀገራት ሲያለመልም የኖረው ታላቁ ዓባይ አምጣ የወለደችው እናቱን ሲያሳዝን ኖሮ አሁን ላይ አደብ ገዝቶ አዲስ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅና ወደ ሥራ መግባት ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም ድህነትን ማሸነፍ እንደሚችሉ ያረጋገጡበት ✊🇪🇹 አዲስ የነፃነት አርማ ነው። ኢትዮጵያ የሌሎችን ጥቅም ሳትጎዳ፣ የራሷን የተፈጥሮ ጸጋ ለልማቷ እና ለሕዝቧ ብልጽግና የመጠቀም መብቷን በጽናት አስከብራለች።

ሀገራዊ ሉዓላዊነቷን እና የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም ሕጋዊ እና ተፈጥሯዊ መብቷን በማረጋገጥ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አጠናቅቃ የዘመናት ሕልሟን እውን አድርጋለች። ከጓሮዋ እሸት 💡🦈መቅጠፍ ጀምራለች። ከራሷ አልፎ ለጎረቤቶቿ ከእሸቱ ቅመሱ ብላለች።

📌በግድቡ ላይ ያላት ዋና መርሕ ግልጽ እና ወጥ ነው። ያላትን የተፈጥሮ ጸጋ የመጠቀም መርሕ። ይህ አቋም የሉዓላዊነት፣ የእኩልነት እና የልማት ጥያቄ እንጂ የማንም ሀገር ጥቅም የመጋፋት ፍላጎት እንዳልኾነ የዓባይ ውኃ በግልጽ ይመሰክራል። ኢትዮጵያም ያላትን አትሰጥም፤ የሌሎችንም አትነካም።

ኢትዮጵያ ከ85 በመቶ በላይ የሚኾነውን የዓባይ ውኃ አስተዋጽእ የምታበረክት ቢኾንም በታሪክ አጋጣሚ ግን ለዘመናት የዚሁ ውኃ ጥመኛ ኾና ቆይታለች። በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ውሎች ኢትዮጵያን ያገለሉ እና ፍጹም ፍትሐዊ ያልበሩ ነበሩ።

🏞በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት መሠረት (CFA – Nile Basin Cooperative Framework Agreement) ግን የተፋሰሱ ሀገራት በፍትሐዊነት የተፈጥሮ ሀብታቸውን የመጠቀም መብት እንዳላቸው ተደንግጓል።

ኢትዮጵያም የማንንም ሳትነካ የራሷን ሀብት ለመጠቀም ሠርታለች። የዓባይ ወንዝ ዛሬም ነገም የፍትሕ፣ የትብብር እና የብርሃን ምልክት ኾኖ ይፈስሳልም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተለያዩ ጊዜያት ሲናገሩ ኢትዮጵያ ማንም ሀገር እንዲጎዳ አትፈልግም፤ ነገር ግን የራሷን የልማት ፍላጎት እና የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብቷን ለድርድር አታቀርብም ብለው ነበር። ግድቡ የአንድነት፣ የጽናት እና የፍትሐዊነት ማሳያ ነውም ማለታቸው ይታወሳል።

የውኃ ሀብት እና የጂኦፖለቲካ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ የሕዳሴው ግድብ የፖለቲካ ፕሮጀክት ሳይኾን የሕልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የራሷን ሀብት አልምታ ለመጠቀም የማንም ፈቃድ አያስፈልጋትም ነው ያሉት።

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በገዛ አቅሟ መገንባት ስትጀምር የታሪክን መዛባት ለማስተካከል እና ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀምን ለማረጋገጥ መኾኑን ለዓለም ያሳየች መኾኑን ነው።

ይህ ያልተዋጠላቸው ሀገራት ግን ብዙ ነበሩ። ምንም እንኳ ዛሬም ድረስ ባይጠፉም። የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ የመልማት መብት እና የውኃ አጠቃቀም ፍትሐዊነት በተመለከተ ዛሬም ድረስ አላስፈላጊ አጀንዳዎችን እየፈጠሩ ነው።

ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ ዋነኛ ምንጭ ኾና እያለች የሕዝቧን የኤሌክትሪክ ፍላጎት🏗 ለማሟላት እና ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት እንደ ስጋት ማየት ከታሪካዊ ስህተት እና ፍትሐዊ ካልኾነ አመለካከት የሚመነጭ ነው።

የቆዩ እና የፍላጎት ስምምነቶችን ብቻ መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያን የልማት መብት ለማደናቀፍ መሞከር የዘመኑን እውነታ አለመረዳት ነው። የሕዳሴውን ግድብ ተፈጥሯዊ የልማት ውጥን ወደ ቀጣናዊ ውጥረት የመቀየር ሙከራ ፍትሐዊነትንም ኾነ የጎረቤት ሀገራትን ዘላቂ ትስስር አይጠቅምም።

የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም ፍትሐዊ መብት መቃወም የሕዝቦቿን የዕድገት እና የብርሃን ፍላጎት መቃወም ነው። እነዚህ አካላት ከቀደምት አግላይ አመለካከቶች ተላቅቀው ወደ የጋራ ተጠቃሚነት እና ትብብር መምጣት ይገባቸዋል።

🎯 ኢትዮጵያውያን ከግድቡ ጋር ተያይዞ ከምንጊዜውም በላይ በንቃት መንቀሳቀስ ይጠበቃባቸዋል። ግድቡ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት እንደመኾኑ መጠን ሀገራዊ አንድነትን፣ መግባባትን ማጠናከር እና ልማቱን መጠበቅ ያስፈልጋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችን በእውነት እና በጠንካራ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ መሞገት እና የሀገርን ትክክለኛ ዕይታ ዲፕሎማሲያዊ በኾነ መንገድ ማሳወቅም ተገቢ ይኾናል።

🌊የግድቡን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የተፋሰስ እንክብካቤ እና የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠልም ሌላው ኢትዮጵያውያን ሊሠሩት የሚገባ ተግባር ነው።

የሕዳሴው ግድብ የመጨረሻው የኢትዮጵያውያን ፕሮጀክት ሳይኾን የሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መነሻ በመኾኑ ሀገራዊ ኢኮኖሚን በራስ አቅም ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እና ለተመሳሳይ የልማት ሥራዎች መዘጋጀትም ያስፈልጋል።

#አሚኮ #GreatEthiopianRenaissanceDam #ኢትዮጵያ #Abay

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

✍️ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleአካባቢን ጽዱ እና ውብ በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ የተመቼች ኢትዮጵያን መገንባት ይገባል።
Next article“ደሜ የአንዲት እናት ሕይዎት ማዳኑ ሲነገረኝ ከፍዬ ያሳከምኩ ያህል ደስታ ተሰምቶኛል”🩸🤱✨