አካባቢን ጽዱ እና ውብ በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ የተመቼች ኢትዮጵያን መገንባት ይገባል።

12

 

የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን
“ጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ”በሚል መሪ መልዕክት ሦሥተኛ ዙር ክልል አቀፍ የአካባቢ ብክለት መከላከል ዘመቻ የንቅናቄ የማስጀመሪያ መረሐ ግብርን በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የፌደራል አካባቢ ጥበቃ ባለ ሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ
መኩሪያ የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ለሦሥት ወራት የሚቆይ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኝ ተግባር መኾኑን ገልጸዋል።

ይህ ንቅናቄ የከተሞችን ገጽታ ከማሻሻል ባለፈ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት እና እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገ መኾኑን ተናግረዋል። በከተማ ደረጃ የሚሠራው የኮሪደር ልማት ትልቅ እንቅስቃሴ እየታየበት ነው ብለዋል።

በቀጣይ ሦሥት ወራትም ፕላስቲኮችን ማስወገድ፣ የኬሚካል አጠቃቀም ቁጥጥር እና የድምጽ ብክለት መከላከል ሥራ ይሠራል ነው ያሉት። ሥራው በቅንጅት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በዚህም ለነገው ትውልድ ጽዱ እና አረንጓዴ ሀገር ማስረከብ ያስፈልጋል ብለዋል። ቆሻሻን እና ፕላስቲክን በዘላቂነት መከላከል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለ ሥልጣን ምክትል ኅላፊ በልስቲ ፈጠነ በክልሉ ለሦሥት ወራት የሚቆይ የጽዳት ዘመቻ መጀመሩን ገልጸዋል። የጽዳት ዘመቻው ጤናማ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ድርሻው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ምንም ዓይነት ጥቅም የሌለው ተደርጎ ይታይ ነበር፤ አሁን ግን በአግባቡ ተሠብሥቦ በራሱ ሀብት መኾኑ ለወጣቶች በሚገባ ማስተማር በመቻሉ በርካታ ወጣቶች በዚህ መስክ ተሰማርተው ገቢ እያገኙ ይገኛሉ ብለዋል።

በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ምዕራፍ ሥራዎች የሚበሠብሥ እና የማይበሠብሥ ቆሻሻ በአግባቡ ተለይቶ እንዲወገድ የማድረግ ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል። በዚህም ከተሞችን ጽዱ እና ውብ ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ350ሺህ ሜትር ኩብ በላይ ደረቅ ቆሻሻ በአግባቡ ተሠብሥቧል፤ በቀጣይም ኅብረተሰቡ ባሕል እንዲያደርገው የአመለካከት ለውጥ የማምጣት ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።

#አሚኮ #CleanEthiopiaForFuture🇪🇹

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

✍️ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleኢትዮጵያውያን ሁሉ ስለአንዲት ሀገራቸው እየመከሩ ነው።
Next article🇪🇹ኢትዮጵያ ያላትን አትሰጥም፤ የሌሎችንም አትነካም