🕊️ ሰላም የሁሉም ድምጽ ናት !

9

 

በአማራ ክልል ከ2015 ዓ.ም መገባደጃ ጀምሮ የተከሰተው የሰላም እጦት ጥሎት ያለፈው ጉዳት ጥልቅ እና ሁለንተናዊ ነው። ክልሉ የሀገሪቱ የግብርና ምርት የጀርባ አጥንት በመኾኑ ግጭቱ የንግድ መስመሮችን ዘግቶ፣ የግብዓት ሥርጭትን አጓድሎ እና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን አቀጭጮ የኑሮ ውድነቱን ለሸማቹ ፈተና እንዲኾን አድርጎት ቆይቷል።

በትምህርት እና በጤና ተቋማት መዘጋት፤ በዜጎች መፈናቀል፣ በትውልዱ ላይ በሰፈነው ስጋት እና ጭንቀት ሳቢያ ማኅበራዊ እና ሥነ-ልቦናዊ መስተጋብሩ ክፉኛ ተጎድቷል። ነገር ግን በዚህ ሁሉ ስጋት ውስጥም ቢኾን የሕዝቡ የሥራ ወኔ እና የማይበገር ተስፋ አልተሰበረም። አርሶ አደሮች እና ነጋዴዎች ላባቸውን እያፈሰሱ ያስመዘገቧቸው የልማት ውጤቶች ለነገው ብሩህ ቀን ያለውን ጽናት የሚያሳዩ ህያው ምስክሮች በመኾን ይነሳሉ።

ችግሩ ጊዜ ሳይወስድ በዘላቂነት መፈታት እንዳለበት የሁሉም ፍላጎት ነው። ችግሮች በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይኾን በጠረጴዛ እንዲፈቱ ቅድሚያ ለዚህ አካሄድ እንዲሰጥ የሰላም ፈላጊው ሕዝብ ጽኑ ፍላጎት ነው።

በሰላም ወጥቶ መግባት የማያሰጋበት ክልል እንዲኾን፤ ልጆቻችን እንዲማሩ፤ የነገ ተስፋችን እንዳይጨልም፤ ያለምንም ስጋት ወደ ልማት ገብተን ያመረትነውን በነጻነት ለገበያ እንድናቀርብ፤ መገዳደል ይብቃን፤ የሰላም አጋዥ ኾነን ሰላማችንን ማረጋገጥ ዋናው ፍላጎታችን የሚሉ ድምጾች በየመድረኩ ተሰምተዋል።

ይህ እውነተኛ እና መሪር ሕዝባዊ ጩኸት አሁን ላይ ፍሬ ማፍራት ጀምሯል፤ በክልሉ ውስጥ የሚነፍሰው የሰላም አየር መሻሻሎችን እያሳየ፤ የጠመንጃ ድምፅ እየቀነሰ የትጥቅ ትግል በቃኝ የሚሉ ድምጾች ጎልተው መሰማት ጀምረዋል።

መንግሥት ይህን አስከፊ ቀውስ ለመቀልበስ:-

👉 የይቅርታ እና የሰላም ጥሪዎችን በተደጋጋሚ በማቅረብ፤ የሰላም ኮሚቴዎችን በማቋቋም እና መሳሪያቸውን በሰላም ለሚያስረክቡ አካላት ማገገሚያ እና ማቋቋሚያ ዕድሎችን በመስጠት የፖለቲካ እና የውይይት አማራጮችን አስቀድሟል።

👉 ሰላማዊ ጥሪዎችን ውድቅ በማድረግ የሕዝቡን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ እና መሰረተ ልማቶችን በኃይል ለመናድ በሞከሩ የታጠቁ ኃይሎች ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃዎችን ወስዷል፤ እየወሰደም ይገኛል። በእነዚህ የተቀናጁ ጥረቶች በአሁኑ ወቅት መደበኛ የትራንስፖርት፣ የንግድ እና የመንግሥት አገልግሎቶች በተለያዩ አካባቢዎች ወደ ቀድሞ መመለሳቸውን የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

የክልሉ ሰላም በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቆም እና ዘላቂ እንዲኾን ግን አሁንም በቅንጅት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በቅርቡ በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ግጭት እና ጦርነት ወደ ድል ስለማይወስድ የመንግሥት ፍላጎት የታጠቁ ወገኖች በድርድር እንዲመለሱ ማድረግ ነው ብለዋል። በአማራ እና በኦሮሚያ ክክሎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ በርካታ ወገኖች የሰላምን አማራጭ መቀበላቸውን ገልጸዋል። ሌሎችም ሰላማዊ የትግል አማራጭን እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።

👉 የታጠቁ ኅይሎች ከመንግሥት የሚቀርቡ የሰላም ጥሪዎችን በመቀበል የሕዝብን ድምጽ በተግባር ማክበራቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል።

👉 የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የአማራ ሕዝብ ያለውን የዳበረ የዕርቅ እና የሽምግልና ባሕላዊ እሴት በመጠቀም ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መሥራት ይገባቸዋል።

👉 የዲያስፖራው ማኅበረሰብ ግጭትን በገንዘብ እና በሀሳብ ከመደገፍ እና ጥላቻን ከማራገብ ወጥቶ ትኩረቱን በክልሉ መልሶ መገንባት፤ ማኅበራዊ ትስስር እና የልማት ድጋፎች ላይ በማድረግ ለገናናዋ ኢትዮጵያ የአማራ ክልል አበርክቶ ከፍ እንዲል ማድረግ ይጠበቅበታል።

በስማቸው አጥናፍ

#አሚኮ_ዜና #ሰላም #አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹 #ባሕር_ዳር #ሐምሌ_16_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከጋና ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ጋር ተወያዩ።
Next article“እድሜ ልክ – ከሰላም የራቁ”