ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከጋና ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ጋር ተወያዩ።

9

 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከጋና ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ጋር በሁለትዮሽ እና በጋራ አህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ከአፍሪካ ኅብረት የጤና ዘርፍ ልዩ የመሪዎች የጤና ጉባኤ በተጓዳኝ ከጋና ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ጋር በጁብሊ ሀውስ በሁለትዮሽ እና በጋራ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከጋና ጋር ከፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መነሻ ጀምሮ ለዘለቀው ታሪካዊ እና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነቷ ትልቅ ሥፍራ ትሰጣለች ነው ያሉት። በአዲስ አበባ የሚገኘው አዲሱ የጋና ኤምባሲ ሕንፃ መጠናቀቅም የሁለቱ ሀገራት የማይናወጥ ወዳጅነት ምልክት መኾኑን በውይይታችን አንስተናል ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ማሃማ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት እና የአንድነት አርማነቷን እንደጠበቀች፣ አሁን ደግሞ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎች የልማት ዘርፎች እያሰመዘገበቻቸው ባሉ አበረታች ለውጦች እና ስኬቶች በእጅጉ መደነቃቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ሀገራችን ለ12ኛ ጊዜ የሚካሄደውን የጣና ፎረም ለማዘጋጀት እያከናወነችው ያለችውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ የሚበረታታ መኾኑን አንስተዋል። በፎረሙ ቦርድ ላይ እያበረከቱ ላሉት እጅግ የላቀ አመራርም የከበረ ምስጋናችንን አቅርበንላቸዋል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

#የኢትዮጵያ_ዲፕሎማሲ

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከሚሠሩ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጋር በጋራ አንሠራም” የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች
Next article🕊️ ሰላም የሁሉም ድምጽ ናት !