“እድሜ ልክ – ከሰላም የራቁ”

12

 

እራሱ ያፈርሳል፣ እራሱም ይከስሳል፣ እራሱ ጸብ ይጭራል፣ እራሱም ሰላም ፈላጊ መስሎ ይመጣል፡፡ ለግማሽ ክፍለ ዘመን የዘለቀ ውሸት፣ ለግማሽ ክፍለ ዘመን የዘለቀ የሰላም ጠልነት፣ ለግማሽ ክፍለ ዘመን የዘለቀ አስመሳይነት፤ ሀገርን መግፋት፣ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ማድማት፡፡

ለግማሽ ክፍለ ዘመን ከውይይት ይልቅ ጦርነትን፣ ከሰላም ይልቅ ግጭትን፣ ከእኛነት ይልቅ እኔነትን ሰብኳል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን መንገድ የሚመራቸው፣ ኢትዮጵያን እንዲያደሙ የሚተባበራቸው፣ ገንጣይ እና የአስገንጣዮችን፣ ነጻ አውጭ ነን የሚሉ ቡድኖችን የሚያስተባብራቸው፣ መሳሪያ የሚያቀብላቸው፣ ከጀርባ ኾኖ የሚያዋጋቸው፣ ከሕዝብ እና ከመንግሥት በተቃራኒ የኾኑ ሃሳቦችን የሚሰጣቸው እርሱ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ አንድነትን በመሸርሸር እና ከፋፋይ አስተሳሰብን በማራመድ ተወዳዳሪ የለውም። ሌሊት የገደላቸውን ጠዋት አጽናኝ ኾኖ ይመጣላቸዋል፤ በዕቅድ ያፈናቀላቸውን መልሶ የሚያቋቁም ቡድን ይልክላቸዋል፤ የሚያሳድዳቸውን ጠባቂያችሁ ነኝ ይላቸዋል፤ በሥርዓት የለያያቸውን አንድነታችሁን ያጠናከርኩት እኔ ነኝ እያለ ይምል ይገዘትባቸዋል፤ በማንነታቸው የሚያጠቃቸውን ማንነታችሁን የጠበኩት እኔ ነኝ እያለ ያፌዝባቸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመኾን ኢትዮጵያን ወግቷል፤ አድምቷል፤ ለሥልጣን ሲል ጥቅሟን አሳልፎ ሰጥቷል፤ ከባሕር የተገፋች፤ ታሪካዊ እርስቷን ያጣች ሀገር አድርጓታል፤ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የጠበቁትን አንድነት፤ ያከበሩትን ኢትዮጵያዊነት በፖለቲካዊ ሥርዓት ሸርሽሯል፡፡ ያለ ግጭት የማያድር፣ ያለ ጦርነት የማይኖር ነው ሕገወጡ ሕወሃት፡፡

ፈተናዎች ያጸኑትን፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሚመኩበትን ሠራዊት የካደው ሕገ ወጡ ሕወሃት ሀገር ላደማ ጦርነት መነሻ ነበር፡፡ በዚያ ጦርነት ኢትዮጵያ ተጎድታለች፡፡ ልጄ ባለችው ተከድታ ደምታለች፡፡

ራሱ በጫረው ጦርነት ተንኮታኩቶ የተሸነፈው ሕገወጡ ቡድን በፕሪቶሪያ ጦርነት በቃኝ፤ ትጥቄን እፈታለሁ፤ የፌዴራል መንግሥቱን ትዕዛዝ እና የሀገሪቱን ሕግ አከብራለሁ ብሎ ተስማምቶ ነበር። አሁን ግን ጊዜ ሲያገኝ መሸነፉን ረስቶ፣ ለምኖ መስማማቱን ዘንግቶ የፕሪቶሪያ ስምምነትን አፍርሶ ለጦርነት እየተዘጋጀ ነው።

የፕሪቶሪያ ስምምነትን ራሱ አፍራሽ ኾኖ ሳለ የፌዴራል መንግሥት እንዳፈረሰው ለማስመሰል ሀሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨት ከጀመረ ሰነባብቷል። ራሱ አፍራሽ፣ ራሱም ከሳሽ የኾነው ሕገወጡ ቡድን ዛሬም እንደ ትናንቱ የማስመሰል እና የማጭበርበር ፖለቲካውን ተያይዞታል። ዳሩ ዛሬ ትናንት አይደለም፤ ትናንት የተሸወዱት ነቅተዋል፤ ትናንት በሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ የታለሉት ዕውነቱን ካወቁት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሕገወጡ ቡድን ዘመንም፣ የፖለቲካ መስመርም ከካዱት እና ከከዱት ቆይተዋል።

ቹቹ አለባቸው ( ዶ.ር) ዳገት ያበረታው የአማራው ፍኖት በተሰኘው መጽሐፋቸው ሕወሃት ከምሥረታው ጀምሮ ሕዝብን ጠላቴ ነው በሚል የተነሳ፣ የብሔር ፖለቲካ በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ያደረገ፣ የኢትዮጵያን አንድነት የፈተነ እና ትግራይን ሀገር አደርጋለሁ ብሎ የተነሳ ነው ይላሉ። ይህ ሕገ ወጥ ቡድን ከትናንት እስካዛሬ ከሰላም እና ከውይይት በስተጀርባ ነው።

በአማራ ክልል በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም በተዘጋጀው የወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት የታፈኑ ዕውነታዎች መጽሐፍ ሕገወጡ የሕወሃት ሥሪት እና የፖለቲካ ባሕል የኢትዮጵያን ፖለቲካ በጥላቻ አየር የተበከለ እና በመጠፋፋት የታጀበ እንዲኾን አድርጎታል ተብሎ ተጽፏል።

ሕገወጡ ሕወሃት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ ኋላ በመጎተት ፍፁም አቻ የለሽ የጥፋት መስመር ነው የተከተለው። ከትጥቅ ትግል ሀገሪቱን እስከ አሥተዳደረበት ዘመን ድረስ የጥላቻ ፖለቲካን በሰፊው ሲያራግብ የኖረ፤ አሁንም ከሥልጣን ተንኮታኩቶ ጥላቻን የሚያራግብ፣ ሕዝብን ለጦርነት እና ለግጭት የሚቀሰቅስ፣ ሰላምን የሚጸየፍ ቡድን ነው።

ከጅምሩ የኢትዮጵያን የጋራ ማንነት ክዶ “ታላቋ ትግራይ” እያለ ስም ላወጣላት ከባቢ የሀገር ምስረታ የተነሳው ሕገወጡ ሕወሃት በዓለም የፖለቲካ ታሪክ የሚጠላውን ሀገር እና ሕዝብ የመራ ብቸኛው ድርጅት መኾኑን በተግባር ራሱን ያጋለጠ ኀይል ነው ይላል፡፡

ከትግራይ ሪፐብሊክ ወደ ትግራይ የበላይነት የተሸጋገረው ሕገወጡ ሕወሃት በአገዛዝ ዘመኑ ኢትዮጵያውያንን ነጣጥሎ ለመግዛት ሰፊ እና አፍራሽ የፕሮፖጋንዳ ስልት ተከትሏል። ሕገወጡ ሕወሃት በሁለመናው የክህደት ድርጅት ነው። ከጥንስሱ ሲጀምር በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያሳየው ክህደት መነሻ ዓላማው ኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ አለን ብለው እንዳይኮሩ፣ ለቀጣዩ በጋራ እንዳይቆሙ እና የአናሳ ገዥነቱን ለማንበር ያለመ ነበር ነው የሚለው፡፡

በዚህ መነሻ የታሪክ ክህደት ፈጽሟል፡፡ በሂደት ራሱ እና እርሱ የሚያግዛቸው ቡድኖች ባደረጉት ቅስቀሳ እና ሕዝብን ለመለያየት በሰሩት ሥራም ንፁሐን ኢትዮጵያውያን ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ተሳድደዋል፤ ተገድለዋል፡፡

ድርጅቱ በሁለንተናዊ ማንነቱ በክህደት ያደገ በመኾኑ አንዳች የሕግ፣ የሞራል፣ የፖለቲካ፣ መርህ አይዳኘውም። በዚህ ባህሪው በግጭት መሐል አትራፊ ኾኖ የኖረ ኀይል ነው፡፡ ሁሉም ድርጅታዊ ውሳኔዎቹም ኾኑ አቋሟቹ ተሻጋሪ ሳይኾኑ አሁናዊ ትርፉን ታሳቢ ያደረጉ መኾናቸው ውለው አድረው ሀገራዊ መዘዝ ሲያመጡ ተስተውሏል።

ከሁሉም በላይ በሕዝብ እና በሀገር ክህደት ዙሪያ የፈፀማቸው ተግባራቱ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ዛሬም ድረስ ለቀጠለ አደጋ ተጋላጭ አድርጓቸዋል፡፡

ሕገወጡ ሕወሃት የሀገር እና ሕዝብ ክብርን የነካ፣ የሀገርን የግዛት አንድነት አደጋ ላይ የጣለ፣ ከውጭ ሀገር ጠላት ጋር የሚተባበር፣ ሉዓላዊነት እንዲጣስ የሚያመቻች፣ ሀገር በውጭ ኀይል እንዲወረር ከውጭ ጠላት ጋር የሚሠራ፣ ሀገር ወደ ጦርነት እንድትገባ የሚገፋፋ እኩይ ድርጅት ነው ይላል መጽሐፉ።

የኢትዮጵያን የረዥም ዘመን የሀገረ መንግሥትነት ታሪክ የካደው ሕገወጡ ሕወሃት ለግዛት አንድነቷ እና ለሉአላዊነቷም ግድ የሚሰጠው ቡድን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ አካል የነበረችው ኤርትራ እንድትገነጠል፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ ያደረገ ነው። ሥልጣን ላይ ኾኖም፣ ከማዕከላዊ መንግሥቱ ሥልጣን ተባርሮም፣ ከፖለቲካ ፓርቲነት ተፍቆም የሽብር ፖለቲካን የሚጠቀም የሀገር እና የሕዝብ ጠላት ነው።

#አሚኮ #Ethiopia #PretoriaAgreement

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_16_2018 ዓ_ም

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🕊️ ሰላም የሁሉም ድምጽ ናት !
Next articleኢትዮጵያውያን ሁሉ ስለአንዲት ሀገራቸው እየመከሩ ነው።