
የኢትዮጵያ ባሕላዊ አልባሳት ጥበብ ከዘመናት በላይ የዘለቀ፣ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ እሴቶችን የያዘ ድንቅ የጥበብ ሥራ ነው።
የሀገራችን ባሕላዊ አልባሳት በተለይም የሐበሻ ቀሚስ እና የጥልፍ ጥበብ የሕዝቦችን ማንነት፣ ውበት፣ ዕይታ እና ጥበብ ለዓለም የገለጡ ናቸው። በዓላት ሲከበሩም የዕለቱ ድምቀቶች ናቸው።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር (የባሕል ጥናት ትምህርት ክፍል) መምህር ተመሥገን በየነ (ዶ.ር) በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በዓላት እና ባሕላዊ አልባሳት ከፍተኛ ማኅበረሰባዊ ቁርኝት እና ትስስር እንዳላቸው ይገልጻሉ። በዓላት ማጌጥን፣ መዋብን እና መኳኳልን የሚያካትቱ ክዋኔዎች በመኾናቸው ከባሕላዊ አልባሳት ጋር ያላቸው ትስስር እጅግ የጠበቀ ነው ይላሉ።
መምህሩ እንዳሉት፣ እነዚህ አልባሳት የማንነት፣ የኩራት፣ የሕዝብ መለያ መገለጫዎች እና የሀገር ከፍታ እና የክብር ማሳያ ናቸው ብለዋል።
በክረምት ወቅት በተለይም በነሐሴ እና መስከረም ወራት የሚከበሩ እንደ ቡሄ፣ ደብረታቦር፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እንግጫ ነቀላ፣ አሱሪቴ እና ሌሎችም ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት ለባሕላዊ አልባሳት ማበብ እና ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው።
በዓላቱ ሲመጡ ወንዶችም ኾኑ ሴቶች የሚለብሷቸው ባሕላዊ አልባሳት ለበዓሉ ድምቀት እና ውበት ልዩ ድባብ ይሰጣሉ።
በበዓላት ወቅት ሰዎች ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ የኾኑ ባሕላዊ አልባሳትን መልበሳቸው በመካከላቸው ያለውን ወዳጅነት እና ማኅበራዊ ትስስር ያጠናክራል ይላሉ።
የጥልፍ ዲዛይኖች፣ የቀለም ቅንጅቶች እና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለዲዛይነሮች እና ከባሕላዊ አልባሳት ጋር ለሚሠሩ ባለሙያዎች ትልቅ የፈጠራ ዕድገት ምንጭ መኾናቸውን ያስረዳሉ። ልብሶቹም ማኅበረሰባዊ መስተጋብርን የመግራት እና የማስተማር ትልቅ አቅም እንዳላቸው ይገልጻሉ።
የጥጥ ፈትል እና የሽመና ውጤቶች ከባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ መስተጋብሮች ጋር በቀጥታ የተሳሰሩ ናቸው። እያንዳንዱ ልብስ የራሱ የኾነ የጥልፍ እና የቀለም ትርጉም እንዳለውም ያነሳሉ።
በተለይም ከልጅ እስከ አዋቂ የሚዋቡባቸው ኩታ፣ ጋቢ፣ ነጠላ፣ ቀሚስ፣ ድሪ እና የተለያዩ ጌጣጌጦች እንደየ አካባቢው እና እንደየ ማኅበረሰቡ የተለየ ትምህርት እና ትርጉም ይሰጣሉ ነው ያሉት ።
የባሕላዊ አልባሳት ከጊዜ ወደጊዜ እያደጉ የመጡ ሲኾን ወጣቶች በተመሳሳይ በባሕል አልባሳት አጊጠው ሲወጡ ይስተዋላሉ። ይህም ለወደፊቱ ትውልድ ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በአምራቾችም በኩል ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ አልባሳትን እያመረቱ ለገበያ ተደራሽ የማድረግ ልምዳቸው እያደገ መኾኑን መታዘባቸውን ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ የጥልፍ እና ቀለም አጣጣል ጥበብ የሀገሪቱን የጥንት ዕደ-ጥበብ በድምቀት የሚያሳይ ነው። የተለያዩ አለባበሶች እና አጊያጊያጦችም የማኅበረሰቡን እሴት እና ማንነት በማንፀባረቅ ለዓለም ማኅበረሰብ የሚያስተዋውቁ እና ትኩረት የሚስቡ ድንቅ ውበቶች ናቸው።
የባሕል አልባሳቶች የበዓል ድምቀቶች፣ ውበቶች እና የሀገር ኩራት በመኾናቸው መጠበቅ እና ማስቀጠል እንደሚገባም ተመላክቷል።
#AMECO EthiopianCulture #HabeshaDress🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_16_2018_ዓ_ም
✍️በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
