“🌊⚖️የዓባይ ፍትሕ፤ የግድቡ እውነት እና የካይሮ ፍርሃት

22

 

​ለዘመናት በቁጭት ሲፈስ የኖረው ዓባይ ዛሬ የኢትዮጵያውያን የብሔራዊ ክብር እና የሕልውና ማዕከል ኾኗል።

ኢትዮጵያ ከ85 በመቶ በላይ የኾነውን የውኃ አስተዋጽኦ ታበረክታለች። ኢትዮጵያ እንዳትጠቀምበት ግብጽ ስታደርገው የኖረችው የዘመናት ጫና ዛሬ ላይ በፍትሐዊነት የመልማት መብት ተሸንፏል።

​👉ግብጽ በዓባይ ላይ ያላት ፍላጎት

​ግብጽ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላት ፍላጎት እና የምታራምደው የውኃ ፖሊሲ የአንድ ወገን የበላይነትን ብቻ መሠረት ያደረገ ነው። የዓለም ዓቀፍ ሕግጋትን የጣሰ፣ የፍትሐዊነት መርሕን ያላከበረ አቋም ነው።

በዓባይ ላይ የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎትን ለመገደብ ከጦርነት እስከ ዲፕሎማሲያዊ ስልት፣ ከፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ዓለም አቀፍ ተቋማትን እስከ መጠምዘዝ የሚዘልቅ ዘርፈ ብዙ ስትራቴጅ ነድፋ ሥትሠራ ቆይታለች።

በተለይም በቅኝ ግዛት ዘመን የተደረጉ እና የላይኞቹን የተፋሰስ ሀገራትን ያላካተቱ አግላይ ውሎችን እንደ ሕጋዊ የመከራከሪያ ሽፋን በማንሳት የዓባይን ውኃ ብቻዋን መጠቀምን እንደ መብት ትቆጥራለች።❌

ዓላማዋም የዓባይን የውኃ ፍሰት ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ ማንኛውንም ልማት እንዳታለማ ማድረግ ነበር።

​👉ግድቡን ለማስቆም የግብጽ ጥረት🚨

ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ መጀመር ይፋ ካደረገችበት ጊዜ ጀምሮ ግብጽ ፕሮጀክቱን ለማስተጓጎል እና ለማስቆም ሁለንተናዊ ጫናዎችን ስታካሂድ ቆይታለች።

ከአረብ ሊግ እስከ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ድረስ ክስ በማቅረብ የዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለማሳደር ሰፊ ጥረት አድርጋለች።

በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር የእርስ በርስ ግጭቶች እንዲስፋፉ በማድረግ፣ ዘርፈ ብዙ የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ እና የጦርነት ዛቻዎችን ጭምር ስትሰነዝር ቆይታለች።

የግብጽን ሕልውና ያሰጋል በሚል የተጋነነ እና የተሳሳተ ስጋት በመፍጠር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ አቋም እንዲይዝ ቀስቅሳለች።

​👉 ኢትዮጵያ የተከተለችው የዲፕሎማሲ ስልት እና የግድቡ ስኬት🕊️

​ኢትዮጵያ የተደቀኑባትን ውስብስብ ጫናዎች ለመመከት የሰላ የዲፕሎማሲ ጥበበ፣ የውስጥ አቅምን እና አንድነትን በማጠናከር ላይ የተመሠረተ ሥራ ሠርታለች።

ኢትዮጵያ “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” የሚለውን መርሕ ተከትላ ለድርድር በሯን ክፍት አድርጋለች። የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የሶስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሾር እንዲካሄድ አቋም በመያዝ የውጭ ኀይሎችን ጣልቃ ገብነት እና ያልተመጣጠነ ጫና በጽናት መክታለች።🇪🇹

የቀድሞው የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሾለሽ በቀለ (ዶ.ር) በጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን አቋም በገለጹበት መድረክ “እዚህ ምክር ቤት ተገኝቶ ያስረዳ የመጀመርያው የውኃ ሚኒስትር ሳልኾን አልቀርም፤ ጉዳዩ ወደ ዚህ ምክር ቤት መምጣቱ በራሱ አግባብ አይደለም፤ ምክንያቱም እየገነባን ያለነው የውኃ ግድብ እንጂ የኒውክሊየር ማብላያ አይደለም” ሲሉ የሞገቱበት ለአብነት ይነሳል።

በዓለም ዓቀፍ የባለሙያዎች ቡድን በማቋቋም የፕሮጀክቱን ጤናማነት እና ፍትሐዊነት በሳይንሳዊ መንገድ በማስጠናት እውነታውን ለማስረዳት ጥረት ስለመደረጉ ሚኒስትሩ መናገራቸውም የሚታወስ ነው።

​👉 የሌሎችን ጥቅም ሳትነካ የራስን ጥቅም ማስከበር

​ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላት አቋም “ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም” በሚሉ ዓለም አቀፍ መርኾዎች ላይ የተመሠረተ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የሌሎች ሀገራትን ጥቅም ሳትጎዳ የመልማት ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ ገልጸዋል። ዓባይን በመገደብ የመጠቀም ጉዳይ ግብጽን ወይም ሱዳንን ለመጉዳት ሳይኾን የሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ለማሻሻል እንደኾነም ያነሳሉ።

ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው የጋራ እድገት እና ትስስር መሠረት የሚጥል መኾኑን ገልጸዋል። በግብጽ እና ሱዳን የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ ያስቀራል፤ የውኃ ፍሰቱን ያስተካክላል፣ የደለል ክምችትን ይቀንሳል።

ኢትዮጵያ የውኃ ሙሌቱን እንኳን ያሳካችው የታችኞቹ ሀገራትን ጥቅም መሠረት በማድረግ በየዓመቱ ክረምትን እየጠበቀች መኾኑን የግብጽን “ውኃ ይቀንሳል” የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ያከሸፈ ነበር።

👉🌐ቀጣናዊ አብሮ የመልማት እሳቤን እውን ማድረግ

ኢትዮጵያ ከግድቡ የምታመነጨውን የኤሌክትሪክ ኀይል ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ለማቅረብ ባላት ቁርጠኝነት ለቀጣናዊ ትስስር እና በትብብር ማደግን በተግባር አሳይታበታለች። የግድቡ መጠናቀቅ ለቀጣናውም የትብብር እና የጋራ ዕድገት መንገድ የከፈተ አዲስ ምዕራፍ ነው።💡

ታዲያ እውነታው ይህ ኾኖ እያለ የቀጠለው የግብጽ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ለምን ይኾን? በሀሳብ መስጫ ሳጥኑ ላይ ሀሳባችሁን ስጡበት👇💬

#አሚኮ #ኢትዮጵያ #GERD #Ethiopia🇪🇹

#ባሕር_ዳር፡ ሐምሌ 16/2018 ዓ

✍️በአሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ተኛውን ዙር ቀሪ ጠቅላላ ምርጫ በአማራ ክልል በስምንት ምርጫ ክልሎች ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡
Next article“ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከሚሠሩ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጋር በጋራ አንሠራም” የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች