
በሀረሪ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 47 አዳዲስ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን የክልሉ ኢንተርፕራይዝ ልማት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ምክትል ኀላፊ ሀምዲ ሰለሃዲን በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ከማሳደግ ባለፈ በዘርፉ ትልቅ መነቃቃት እየፈጠረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት 47 መካከለኛ እና አነስተኛ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንደገቡም ተናግረዋል። ተጨማሪ 16 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ የግንባታ ሥራቸውን አጠናቅቀው ወደ ማሽነሪ ተከላ ሥራ መግባታቸውንም አንስተዋል።
በክልሉ ወደ ሥራ የገቡት ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጪ ምንዛሬን ከማስቀረት አንጻር ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ባለፈው ዓመት በኢንዱስትሪ ዘርፉ ብቻ 3 ሺህ 935 ለሚኾኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯልም ብለዋል።
በቀጣይም የኢንዱስትሪ ዘርፉን የማጎልበት ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
